Sunday, March 30, 2014

የማን መጨረሻ? የማኅበረ ቅዱሳን? ወይስ… የኢህአዴግ የመጨረሻ መጀመሪያ?



  • አቶ መለስ ዜናዊና አቦይ ጸሀዬ ከደርግ በተሰነዘረባቸው ጥቃት ገዳማውያን አባቶች የመነኮሳትን ልብስ በማልበስ ከሞት አድነዋቸዋል፡፡(ደርሶ ጡት ነካሽ ቢሆኑም)
  • ‹‹ቤተ ክርስቲያኗ ተከታዮቿን፣ ለነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲገዙ ከማስተማር በዘለለ የብሔራዊ ንቃት(ማንነት) ማስተማርያም ነበረች፡፡ ዶ/ር አረጋዊ
  • ‹‹መንግሥት ያግዘኛል ብዬ ነው እዚህ መንበር ላይ የተቀመጥኩት፤ ባያግዘኝ ሥልጣኑን አልቀበልም ነበር›› አቡነ ማትያስ
  • ፓትርያርኩ  የመዘንጋት፣ ለውሳኔ የመቸገር፣ ዕንቅልፍ የማብዛትና መሰል ችግሮች ሥራቸውን እያስተጓጎሉባቸው እንደኾነ ይነገራል፤ ራሳቸውም ‹‹ሲጨንቀኝ እተኛለኹ፤ ስተኛ ደግሞ እረሳዋለሁ›› በማለት ችግሩን አምነው ተቀብለዋል፡፡
  • ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን ይመለከታል›› በሚል ርእስ ለደኅንነቱ ዋና መሥ/ቤት የተላከ ደብዳቤ…(ያንቡት)
  • ‹‹እናቋርጣለን፤ ነገር ግንእናንተ የጸጥታ ስጋት አለብላችሁ በደብዳቤ ሓላፊነቱን ውሰዱ፡፡ እኛም ለካህናቱ ለምእመናኑ ሁኔታውን ዘርዝረን እንገልጻለን›› አቡነ እስጢፋኖስ መዋቅራዊ ጥናቱ ይቁም በማለት ለመጣ የመንግሥት ካድሬ ሰጡት መልስ…

(አንድ አድርገን መጋቢት 21 ዓ.ም 2006 ዓ.ም)፡-ይህ ጽሑፍ በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ  ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን የመጨረሻዎቹ ቀናት›› በሚል የቀረበ ሲሆን ‹አንድ አድርገን› የተሰጠው አርዕሱን ብቻ በመቀየር የጸሐፊውን ሙሉ ጽሑፉን እንደወረደ ለአንባቢያን አንዲህ አቅርበዋለች፡፡ ጽሑፉ እንዲህ ቀርቧል ፤ ሌላውን ነገር ለአንባቢ ትተናል…

‹‹ማኅበረ ወያኔ››
በኰሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የሚመራው መንግሥት ከናቅፋ እስከ ጉና ተራራ ያሉ ምሽጎቻቸውን ከሰማይ በጦር አውሮፕላን፣ ከምድር እሳት በሚያዘንቡ .ኤሞችና መድፎች ሳያቋርጥ ቢደበድብም በሀገሪቱ ሰሜናዊ አካባቢ ከቀን ወደ ቀን ግዛታቸውን እያሰፉ የተጠናከሩት ‹‹ወንበዴዎች›› ራስ ምራት ኾነውበታል፡፡ የኤርትራ ‹‹ነጻ አውጭ›› ቤዝ-ዓምባው በተወሰነ መልኩም ቢኾን ለጥቃት የመጋለጥ ዕድሉ አናሳ በኾነው የሳህል በርሓ በመኾኑ አብዛኛው የአመራር አባል መሸሸጊያ አድርጎታል፡፡


በተመሳሳይ መልኩ በትግራይ አካባቢ የሚንቀሳቀሱት የወያኔ መሪዎች ምሽጋቸው እንደ ሳህል ምቹ ባለመሆኑ፣ በርካታ ክፉ ቀናትን ካሳለፉባቸው ቦታዎች መካከል በተራራማ አካባቢዎች በሚገኙ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ገዳማት ውስጥ መደበቅ እንደሆነና በየስፍራው መዘዋወር ሲፈልጉም ራሳቸውን ከሚሰውሩባቸው ዘዴዎች ውስጥ በቀሳውስቱና መነኰሳቱ አልባሳት መጠቀም አንዱ እንደነበር በትግሉ ዙሪያ የተዘጋጁ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ በተለይም ታጋይ መለስ ዜናዊ ፤ ኣባይ ፀሃዬ ፤ ግደይ ዘርአጽዮን  ስዩም መስፍን ፤ ስብሀት ነጋን የመሳሰሉ  የአመራር አባላቱ የገዳማቱ ቤተኛ ነበሩ፡፡ከዚሁ ጋር ተየይዞ የሚነገር ታሪክ አለ ፤ የመንግሥት ጸጥታ ሰራተኞች ሁለት የ‹‹ወንበዴ›. መሪዎች በትግራይ በሚገኝ አንድ ገዳም  ውስጥ ከመነኮሳት ጋር ተመሳስለው መሸሸጋቸውን መረጃ ይደርሳቸውና በጥቂት ሰዓታት ውስጥ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ወታደሮችን በመላክ  ዙሪያ ከበባ ያደርጋሉ፡፡ ይህን መደበቂያ በመስጠት የረዷቸው ሁለቱን ታጋዮች ‹‹ወይባ›› በመባል የሚታወቀውን ረዥሙን ቀሚሳቸውን አልብሰው እና ቆብ አስደፍተው ከአካባባው በማሸሽ ይታደጓቸዋል፡፡ የታሪኩ ባለቤት መለስ ዜናዊና አቦይ ጸሀዬ ነበሩ፡፡ በእርግጥ እነዚህ የ‹‹ወንበዴ›› መሪዎች ‹በእንዲህ አይነቱ ከመርፌ አይን እጅግ በጠበበ  ዕድል ህይወታቸውን ከሞት መንጋጋ ተርፎ ኮለኔል መንግሥቱ በጓሮ በር  ወደ ዙንባብዌ ሸኝተን በትረ መንግሥቱን ለመጨበጥና ለሃያ ምናምን ዓመታት ኢትዮጵያን ታህል ታላቅ ሀገር አንቀጥቅጦ ለመግዛት እንበቃለን› የሚል ጠንካራ እምነትና የእርግጠኝነት ስሜት በወቅቱ ነበራቸው ብሎ ማሰብ ለእነርሱም ቢሆን እጅግ አዳጋች ይመስለኛል ፤ የሆነው ግን ይህ ነበር፡፡

‹‹ማኅበረ ቅዱሳን››
መለስ ዜናዊና ጓዶቹ በለስ ቀንቷቸው ባልጠበቁት ፍጥነት የመንግሥት ‹‹ጠንካራ ይዞታ›› የሚባሉ ከተሞችን ሳይቀር እየተቆጣጠሩ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጉትን ግሥጋሴ ሲያፋጥኑ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ደግሞ በመንግሥቱ ኃይለማርያም ሰብሳቢነት፣ በደኅንነት ሠራተኞችና በኢሠፓ ካድሬዎች ገፋፊነት ትምህርታቸውን አቋርጠው ለወታደራዊ ሥልጠና ደቡብ ኢትዮጵያ ወደሚገኘው ብላቴ የጦር ማሠልጠኛ ከተቱ፤ ዩኒቨርስቲውም ተዘጋ፡፡

…………ከመላው ዘማቾች አስራ ሁለት የሚሆኑ ተማሪዎች ተሰብስበው ሲያበቁ በየቀኑ በካምፓቸው አቅራቢያ ወደሚገኝው ሚካኤል ቤተክርስቲያን በመሄድ ከመዓቱ ይታደጋቸው ዘንድ ፈጣሪያቸውን በጸሎት መማጸን የህይወታቸው አካል አደረጉት ፡፡ ከቀናት በኋላ በአንዱ ዕለት አንድም ለመታሰቢያና ለበረከት፣ ለትም ስብስቡ ሳይበተን ወደፊት እንዲቀጥል በሚል እሳቤ ‹‹ማኅበረ ሚካኤል›› ብለው የሰየሙትን የጽዋ ማኅበር መሠረቱ፡፡ይሁንና ከመካከላቸው አንዳቸውም እንኳ 1977 .. በ‹ፓዌ መተከል› ዞን የተደረገውን የ‹መልሶ ማቋቋም› ፕሮግራም እንዲያመቻቹ በዘመቱ ተማሪዎች ከተመሠረተውና ቅዱሳን ከሚዘከሩባቸው ሌሎች የጽዋ ማኅበራት ጋር በመዋሐድ የዛሬውን ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን›› እንደሚፈጥሩ መገመት የሚችሉበት የነቢይነት ጸጋ አልነበራቸውም፤ የሆነው ግን እንዲያ ነበር፡፡

ሃይማኖትን ጠቅልሎ የመያዝ ዕቅድ
በትጥቅ ትግሉ ወቅት የህወሓት አመራር ገዳማትን ለመሸሸጊያነት ብቻ ሳይኾን ለሥልጣን እርካብ መወጣጫነትም ጭምር ተጠቅሞባቸዋል፡፡ ከድርጅቱ መሥራቾች አንዱ አረጋዊ በርሄ ለዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ “The Origin of TPLF” በሚል ርእስ ሠርቶት ኋላ ወደ መጽሐፍ በቀየረው የጥናት ጽሑፉ ላይ ‹‹የቤተ ክርስቲያኗ ሥልጣን (በትግራይ የነበረውን) ለማድቀቅ ሲባል በስብሃት ነጋ የሚመራ የስለያ ቡድን ተቋቋመ፡፡ ይህ ቡድንም ደብረ ዳሞን ጨምሮ በትግራይ ውስጥ ባሉ ገዳማት አባላቱን መነኰሳት በማስመሰል፣ የገዳማቱን እንቅስቃሴ በህወሓት ፍላጎት ሥር የማስገዛት ሥራ ሠርቷል›› ሲል በገጽ 317 ላይ ገልጧል፡፡ ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ ሃይማኖትን ጠቅልሎ ለመያዝ የተነሣበትን ገፊ ምክንያትም እንዲህ በማለት አብራርቷል፡-

‹‹ቤተ ክርስቲያኗ ተከታዮቿን፣ ለነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲገዙ ከማስተማር በዘለለ የብሔራዊ ንቃት(ማንነት) ማስተማርያም ነበረች፡፡ለህወሓት እንቅስቃሴ ዕንቅፋት እንደነበረች ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያኒቱን በህወሓት ዓላማ ሥር ለማሳደር ፍላጎት ነበር፤ በዚህ የተነሣም የእርስዋን ተጽዕኖ ለማግለል ጥልቅ ርምጃ ወስደዋል፡፡›› (ገጽ 315 – 316)
/ አረጋዊ ‹‹ጥልቅ ርምጃዎች›› ብሎ ከጠቀሳቸው መካከል አንደኛው ‹‹ለአጥቢያ ቀሳውስቱ ኮንፈረንስ በማዘጋጀት፣ በትግራይ ውስጥ ያሉትን አብያተ ክርስቲያን ለብቻ ነጥሎ ህወሓት በሚያራምደው የትግራይ ብሔርተኝነት ስር ማካተት›› እንደነበረ በዚሁ መጽሐፍ ጠቅሷል፡፡ ይሁንና አስገምጋሚ መብረቅ የወረደብን ያህል የምንደነግጠው፣ ዶክተሩ ከዚሁ ጋራ አያይዞ ‹‹የተጨቆነው የትግራይ ብሔርተኝነት የተነሣሣውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ተጽዕኖ ለመገዳደር ነው›› በማለት መመስከሩን ስናነብ ነው፡፡ የአረጋዊ መረጃ የሰሚ-ሰሚ ወይም በቢሆን ሐሳብ የተቃኘ አይደለም፤ ይልቁንም ራሱን በመሪነትና ሐሳብ በማዋጣት ከተሳተፈበት ከድርጅቱ የፖሊቲካ ፕሮግራም የተቀዳ እንጂ፡፡

የሆነው ህወሓት 1970-72 .. ድረስ ባሠለጠናቸው ካድሬ ‹‹ካህናት›› አማካይነት ‹‹ነጻ በወጡ›› መሬቶች ላይ ራሱን የቻለ የቤተ ክህነት አስተዳደር (ኖዶስ የተገነጠለ) መመሥረቱ ይታወሳል፡፡ ድርጅቱ ለእኒዚህ ቤተ ክርስቲያን መተዳደርያ ደንብ ከመቅረፅ አልፎ ዓላማውንም እንደ ዓሥርቱ ትእዛዛት በፍጹም ልባቸው የተቀበሉ ‹‹መንፈሳዊ ክንፍ›› አድርጓቸው እንደነበረ አረጋዊ በርሄ ተንትኖ አስረድቷል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሰርጎ ገብነት በእስልምና ላይም መተግበሩ አይዘነጋም፡፡ በተለይም የእምነቱ ተከታዮች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ወላጆቻቸው ሙስሊም የሆኑ ታጋዮችን እየመረጠና ከክርስቲያን ቤተሰብ የወጡ ካድሬዎችንም ሐሰተኛ የሙስሊም ስም እየሰጠየትግሉ ዓላማ እስልምናን ማስፋፋትእንደሆነ በመግለጽ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ይሠራ ነበር፡፡ በዚህ ስልቱ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የአንዳንድ ዓረብ አገራትን ቀልብ ማግኘት ችሏል፡፡ ይህ ደግሞ ከዓረቦቹ በገፍ ርዳታ ያጎረፈለት ሲኾን ወደ መሃል አገር የሚያደርገውን ጉዞም አፋጥኖለታል፡፡

ከመንግሥት ለውጥ በኋላም ሁለቱንም እምነቶች የተቆጣጠረው በታጋይና ምልምልካህናትእናሼኾችለመኾኑ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ዛሬም በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት የበላይ የሆነው ጠቅላይ ቤተ ክህነት ውስጥ ከሚገኙ ሥራ ስምንት መምሪያዎች ውስጥ አሥራ ስድስት በህወሓት ሰዎች የመያዛቸው ኩነት ስልቱ በተሳካ ኹኔታ መተግበሩን ያስረግጣል፡፡ በተለይ ዋነኛው ሰው ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ሲኖዶሱን ብቻ በሚመለከት ጉዳይ ላይ ጭምር ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት ‹‹የመንግሥት ባለሥልጣናትን ላማክር›› ሲሉ በተደጋጋሚ መደመጣቸው እና አንዳንድ ጳጳሳት ተቃውሞ በሰነዘሩባቸው ቁጥር ‹‹መንግሥት ያግዘኛል ብዬ ነው እዚህ መንበር ላይ የተቀመጥኩት፤ ባያግዘኝ ሥልጣኑን አልቀበልም ነበር›› በማለት በግላጭ ሲመልሱ መስተዋላቸው ለሥርዓቱ ተጽዕኖና ጣልቃ ገብነት እንደማሳያ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ከዚህ ቀደም ሦስት ወር የቋሚ ሲኖዶሱ አባል ሆነው የሠሩ አንድ ጳጳስም ‹‹ልጊዜ ቋሚ ሲኖዶሱ ሲሰበሰብ እርሳቸው(ፓትርያርኩ) መንግሥት እንዲህ አለመንግሥት ሳይፈቅድ›… የሚል ንግግር ይጠቀማሉ›› በማለት ፋክት አስተያየት ሰጥተዋል(በነገራችን ላይ ፓትርያርኩ  የመዘንጋት፣ ለውሳኔ የመቸገር፣ ዕንቅልፍ የማብዛትና መሰል ችግሮች ሥራቸውን እያስተጓጎሉባቸው እንደኾነ ይነገራል፤ ራሳቸውም ‹‹ሲጨንቀኝ እተኛለኹ፤ ስተኛ ደግሞ እረሳዋለሁ›› በማለት ችግሩን አምነው ተቀብለዋል፡፡)

በእስልምና እምነት ውስጥም የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ከቀድሞው መጅሊስ የባሰ እንደሆነ በርካታ ሙስሊም ምዕመናን የሚያውቁት እውነታ ነው፡፡ ይህ መጅሊስ የሚዘወረው እንደተለመደው በምክትል ፕሬዝዳንቶች ሲሆን፣ ይህች ዓይነቱ ጫዎታ ደግሞ ህወሓት ጥርሱን የነቀለበት ስለመኾኑ ነጋሪ አያሻም፡፡ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሼኽ ከድር 17 ዓመታት የትግራይ ክልል መጅሊስና የሸሪአ /ቤቱን ደርበው በመያዝ ምእመናኑን ቀጥቅጠው ሲገዙ ከመቆየታቸውም በላይ ታጋይ እንደነበሩ በኩራት ለመናገር እንደሚደፍሩ የቅርብ ሰዎቻቸው ይመሰክራሉ፡፡ በአናቱም ከታጋይ የመረጃ ምንጭ ባይረጋገጥም የመጅሊሱ ፕሬዝዳንት ሼኽ ኪያር መሐመድ ከእኚኹ ታጋይ ምክትላቸው ጋራ በአንዳንድ ጉዳዮች መስማማት ባለመቻላቸውና ‹‹መንግሥት የሚያዘውን ሁሉ ለመሥራት ለምን እንገደዳለን?›› የሚል ተቃውሞ እስከ ማሰማት በመድረሳቸው በቅርቡ ከሓላፊነታቸው ሊነሡ እንደሚችሉ ተወርቷል፡፡

ኢሕአዴግ እና ‹‹መንፈሳዊ ገበያው››
ግንባሩ የእምነት ተቋማትን በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ጠርንፎ መያዝን እንደ ዋነኛ ዓላማ አድርጎ የመንቀሳቀሱ መግፍኤ ከሦስት ጉዳዮች አንጻር በአዲስ መሥመር ለመተንተን እሞክራለሁ፡-
  1.  የመጀመሪያው÷ ቤተ ክህነት በነገሥታቱ ዘመን የነበራትን ፖሊቲካዊ ተሰሚነት (ምንም እንኳ ራሱ ኢሕአዴግም በአፋዊነት ከማውገዝ ቸል ባይልም) ለቅቡልነት መጠቀሚያ የማድረግ ፍላጎቱ ነው፡፡ በገቢር እንደታየውም በኃይል በተቆጣጠራቸውም ካድሬዎቹ ሊደርሱባቸው በማይችሉ የገጠር ቀበሌዎች ተቀባይነት ለማግኘት ማኅበራዊ ተቀባይነት ባላቸው ሼኾች፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት ሲቀሰቅስ በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡ እንዲሁም የእስልምና እምነት በታሪክ ያሳለፈውን አገዛዛዊ ጭቆናን ይኹን የደርጉን ሉንም ሃይማኖት ማግለልን በማጎን ለፕሮፓጋንዳ ተጠቅሞበታል (በወቅቱ የድርጅቱ አመራር አባል የነበሩት አቶ ገብሩ ኣስራት እንደ ሼኾች በመልበስና በመጠምጠም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ብዙኃኑ ታጋዮች አይዘነጉትም) በዚኽ ዘመንም በአብያተ እምነቶች ካድሬ ጳጳሳትንና ካድሬ ሼኾችን አሰርጎ የማስገባቱ ምሥጢር ይኸው ነው፡፡
  2.    እንደ ኹለተኛ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው÷ የታገለለትን ዘውግ ተኰር ፖሊቲካ ያለአንዳች ተግዳሮት ማሳለጥን ታሳቢ ማድረጉ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም የሁሉም ሃይማኖቶች ‹‹የሰው ልጆች በሙሉ የአንድ አምላ ፍጡሮች ናቸው›› በሚል አስተምህሮ የሚመሩ ከመኾናቸው አኳያ፣ ማንነታቸውን በዘውግ ከፋፍሎ ማስተዳደርን ቀላል አያደርገውምና ነው፡፡ ስለዚኽም መፍትሔው አክራሪ ብሔርተኛመንፈሳውያንበየእምነቱ ተቋማቱ እንዲፈለፈሉና ከፍተኛውን የሥልጣን ዕርከን መቆጣጠር እንዲችሉ በማብቃት ላይ የተመሠረተ ብቻ መኾኑን የህወሓት መሪዎች ያውቃሉ፡፡ይህዕውቀታቸው›ም ይመስለኛል ሀገራዊ ስሜት የሌላቸው፣ በችሎታ ማነስና በሥነ ምግባር ጉድለት የሚታወቁ፣ እንዲሁም በእምነት አቋማቸው በተከታዮች ዘንድ ተኣማኒና ቅቡል ያልኾኑ ሰዎች ቦታውን እንዲይዙ እስከ ማድረግ ያደረሳቸው፡፡ የራሳቸው የስለላ መዋቅርም ጥቅምት 2 ቀን 1995 .. ‹‹ለዋናው መሥሪያ ቤት፣ አዲስ አበባ፤ -.ዮ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን ይመለከታል›› በሚል ርእስ ለደኅንነቱ ዋና መሥ/ቤት በላከው ጥናታዊ ዘገባ ላይ እውነታውን እንዲኽ ሲል ገልጾታል፡-
‹‹ለፓትርያርኩ ወዳጅነት አላቸው የሚባሉ ሊቃነ ጳጳሳት ከሦስትና አራት ብዙም ያልበለጡ ናቸው፡፡ ፓትርያርኩ ምንም ዓይነት ተቀባይነትና ከበሬታ ያጡ በመሆናቸው ህልውናቸውን የአንዳንድ መሪዎችን ስም በመጥራትና እንደ ማስፈራሪያ በመጠቀም ላይ የተንጠለጠለ ኾኗል፡፡›› ከዚህ ሪፖርት በኋላም እንኳ በቀጣዩ ሢመት ለማስተካከል አለመሞከሩ መከራከሪያውን አምነን እንድንቀበል ያስገደድናል፡፡ 

3 . ገዛዙ መንፈሳዊ ተቋማትን ጠቅልሎ ለመያዝ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ በሦስተኛነት ሊጠቀስ የሚችለው ምክንያት፣ ምንም እንኳ ተሳክቷል ሊባል ባይቻልም፣ በሥነ ምግባር መታነፅ፣ በአገር አንድነት ማመን፣ ለሕዝብ ጥቅም መቆም፣ የትኛውንም ሕገ ወጥነት ለምን ብሎ መጠየቅና መሰል መንፈሳዊ አስተምህሮዎችን መርሑ አድርጎ የሚነሣ ትውልድ እንዳይፈጠር መከላከልን ታሳቢ አድርጎ እየሠራ ያለውን ሤራ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም የሥርዓቱ ሰዎች በዚህ መልኩ የሚቀረፅ ትውልድን ዛሬ ባነበሩት የጭቆና ቀንበር ለተራዘሙ ዓመታት መግዛት ከባድ እንደኾነ ለመረዳት አይሳናቸውምና ነው፡፡ከዚሁ ጋራ አንሥተን ማለፍ ያለብን ጭብጥ መቃብር ከሚቆፈርለት የኢትዮጵዊ ብሔርተኝነት ጋራ የሚያያዝ ነው ፤ የሃይማኖቱና የማእከላዊ መንግሥቱ የቅድመአብዮቱ ጋብቻ (በምንም ዓይነት መከራከርያ ልንሟገትለት ባንችልም) ቤተ ክርስቲያኒቱ ለኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነቱ ብያኔ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጓን አያስክደንም፡፡ ይህምየሃይማኖቱን ተቋም የብሔርተኝነቱ ወካይ ሆኖ እንዲታሰብ ይገፋዋልብሎ ለሚያምነው ህወሓት፣ ሃይማኖቱ ተቋማዊ ነጻነት እንዳይኖረው የሚቻለውን ኹሉ ሲያደርግ፣ ሃይማኖቱን በማዳከም የብሔርተኝነት መንፈሱንም ማላላት ይቻላል ከሚል መነሾ ነው ብሎ መደምደም ተምኔታዊ አያስብልም፡፡

ገደል አፋፍ የቆመው ማኅበረ ቅዱሳን…
ሥርዓቱ የሃይማኖት ተቋማቱንና መንፈሳዊ መሪዎቹን ለመቆጣጠር ገፊ ምክንያቶች ኾነውታል ብዬ ከላይ ለማብራራት የሞከርኋቸውን ሦስት ምክንያቶች ሙሉ ለሙሉ መተግበርን አስቸጋሪ ያደረጉበት፣ በቀጥታ በምእመናኑ የተመሠረቱ ማኅበራት መኾናቸውን መገመት ይቻላል፡፡ ለማስረጃም ያኽል ከኦርቶዶክስ ክርስትናማኅበረ ቅዱሳን፣ ከእስልምና ያለፉትን ኹለት ዓመታት የእምነቱ ተከታዮች ወካይ ኾኖ የተመረጠው ኮሚቴ አባላት መንግሥትንም ኾነ መጅሊሱን በመገዳደር ያደረጉትን አበርክቶ መጥቀስ ይቻላል፡፡ይሁንና የሙስሊሙን ተወካዮች በገፍ ሰብስቦ እስር ቤት ካጎረ በኋላ፣ ከሲኖዶሱም ኾነ መሰል ማኅበራት ጠንካራ እንደኾነ የሚነገርለትን ማኅበረ ቅዱሳንን ዋነኛ ዒላማ አድርጎ ለመደፍጠጥ የቆረጠ ይመስላል፡፡ የማኅበሩ አባላት በዓለማዊ/ዘመናዊ ዕውቀት የተራቀቁ፣ በሀገራዊ አንድነት ፈጽሞ የማይደራደሩ፣ በጥቅመኝነት የማይደለሉየመኾናቸው ጉዳይ አገዛዙ ከኃይል አማራጭ የቀለለ መፍትሔ የለም ብሎ እንዲያምን አድርጎታል ብዬ አስባለኹ፡፡

በርግጥ በአቶ መለስ ይዘጋጅ እንደነበር ከኅልፈቱ በኋላ በይፋ በተነገረለት የኢሕአዴግ የንድፈ ሐሳብ መጽሔትአዲስ ራዕይ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አብዛኛውን ጊዜ ‹‹የከሰሩ ፖሊቲከኞች፣ ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት፤ አንድ ሃይማኖት አንድ ሀገር እና ሙስሊም ማኅበረሰብ ቀደም ሲል ሲደርስበት የነበረውን በደል በማራገብና በመቀስቀስ፣ ከዚኽም አልፎ ተገቢነት የሌላቸው አዳዲስ ጥያቄዎች በማቅረብ ለማነሣሣትና ለማተረማመስ ሲሠሩ ማየት የተለመደ ሆኗል›› በማለት ከሚያቀርበው የሾላ በድፍን ፍረጃ ዘልሎ መንፈሳውን ማኅበራትን በስም ጠቅሶ ያወገዘባቸው አጋጣሚዎች ብዙም አልነበሩም፡፡ዛሬ ዛሬ ግን ማንኛውንም ሃይማኖታዊ የመብት ጥያቄን ‹‹ወሃቢያም ይኹን ማኅበረ ቅዱሳን…›› በማለት ማውገዙ የተለመደ ኾኗል፡፡ ከውግዘትም ተሻግሮ ጥያቄዎቻቸውን በሕጋዊ መንገድ ወደ አደባባይ ያወጡትን የሙስሊሙን ተወካዮች ሰብስቦ አስሯል፤ በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ሰላማዊ ተቃውሞዎችንም በማስታከክ በበርካታ የእምነቱ ተከታዮች ላይ ግድያና ሥቅየትን ጨምሮ ብዙ ግፍ በመፈጸም ጉዳዩን በጠመንጃ ብቻ የሚፈታ አድርጎ ካወሳሰበው ሰነባብቷል፡፡

‹‹ቀጣዩ የኢሕአዴግ ዒላማ ማኅበረ ቅዱሳን ይኾን?›› በሚል ከስድስት ወራት በፊት በዚኹ መጽሔት ላይ ለማተት እንደሞከርኁት ኹሉ፣ ከላይ በተዘረዘሩ የፖሊቲካ አጀንዳዎችና በሚቀጥለው ዓመት የሚካሔደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ በለመደው የማጭበርበር መንገድ አሸንፎ ያለኮሽታ የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ዓለማዊ ይኹን መንፈሳዊ ነጻ ተቋማት እንዳይኖሩ በይፋ -ሕገ መንግሥታዊ ድርጊቶችን እየፈጸመ ያለው የእነ ኣባይበረከት መንግሥት፣ በአኹኑ ወቅት ሙሉ ትኩረቱን በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ማድረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህን አፈና ለማሳካትም ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ በፍጹም ልባቸው ከመተባበር ለአፍታም እንደማያመነቱ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያኽል አንዱን በአዲስ መሥመር ላቅርብ፡-

ከወራት በፊት የአዲስ አበባ /ስብከት አስተዳደርን ወደ ዘመናዊነት ለማሻገር ሲኖዶሱ ጥናት ተደርጎ እንዲቀርብለት ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡ እናም ጥናቱ ተጠናቆ አገልጋዩና ምእመኑ እንዲወያይበት ሲኖዶሱ በሰጠው አቅጣጫ መሠረት ከኹሉም አድባራትና ገዳማት የተውጣጡ 2700 ሰዎች የተሳተፉበትና በድምሩ አስራ አራት ቀናት የፈጀ ውይይት ይጠራል፡፡ በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ አቡነ እስጢፋኖስ አማካይነት በተመራውና ጥናቱን በሠራው የባለሞያ ቡድን ፈጻሚነት የተከናወነው ውይይት ሲካሔድ በነበረባቸው በመጨረሻዎቹ ሳምንታት በአንዱ ቀንከአንዳንድ የአድባራት አስተዳዳሪዎች ብርቱ ተቃውሞ አጋጥሟልመባሉን ተከትሎ በሊቀ ጳጳሱና በፓትርያርኩ መካከል የሚከተለው ውዝግብ መካሔዱን ሰምቻለኹ፡-

ፓትርያርኩ፡- ‹‹ጥናቱን የሚሠሩት ባለሞያዎች ናቸው ብለውኝ አልነበረም ወይ?››
አቡነ እስጢፋኖስ ፡- ‹‹አዎ! ታዲያስ ባለሞያዎች ናቸው የሠሩት››

‹‹አይደለም! የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ናቸው፤ እርስዎ አታለውኛል!››
‹‹
የጥናት ኮሚቴው አባላት በቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸውና በየአጥቢያው ባላቸው ተሳትፎ ተጠርተው የመጡ ሞያቸውን ዓሥራት ያደረጉ ናቸው፡፡››

‹‹በፍጹም ጥናቱ የማኅበረ ቅዱሳን ነው!››
‹‹
ቅዱስ አባታችን ቢኾንስ፣ ከጠቀመን ችግሩ ምንድን ነው?››

‹‹በቃ! ውይይቱ ከመንግሥት ይቋረጥ ተብሏል፡፡››
‹‹
ለምን ይቋረጣል?››

‹‹የጥናቱ ተቃዋሚዎች ረብሻ ያስነሣሉና የጸጥታ ስጋት አለ››
‹‹
ለምንድን ነው ረብሻ የሚያስነሡት? ከፈለጉ መጥተው መሳተፍ ይችላሉ፤ እኛ እየተወያየን አይደለም እንዴ! ተቃውሞ ያለው መጥቶ ሐሳቡን ይግለጽ እንጂ ማቋረጥ እንዴት መፍትሔ ይኾናል? ደግሞስ ሲኖዶሱ አይደለም ሰነዱ ወደ ታች ወርዶ ይተችበት ብሎ የወሰነው?››

‹‹የለም! ይቁም ተብሏል፤ ይቁም!››
‹‹
እንግዲያስ የከለከለው አካል ራሱ መጥቶ ይንገረን፡፡››

….. የስልክ ምልልሱ ከተጠናቀቀ ከሰዓታት በኋላ አንድ ባለሥልጣን ቢሮ ድረስ መጥቶ፣ ትእዛዙን ያስተላለፈውን አካል ገልጾ ውይይቱ እንዲቋረጥ አሳሰባቸው፤ እርሳቸውም ‹‹እናቋርጣለን፤ ነገር ግንእናንተ የጸጥታ ስጋት አለብላችሁ በደብዳቤ ሓላፊነቱን ውሰዱ፡፡ እኛም ለካህናቱ ለምእመናኑ ሁኔታውን ዘርዝረን እንገልጻለን›› የሚል ምላሽ ሰጥተው ይሸኙታል፡፡ ከዚህ በኋላ እንግዲህ ውይይቱ ይቋረጥ እንግዲህ ለጊዜው ግልጽ ባልሆነ አንድ ምክንያት መንግስት ‹‹ይቋረጥ›› የሚለውን ማስፈራሪያ ማንሳት ያቻለው፡፡ ኩነቱ ግን ፓትርያርኩ ማኅበሩን በጥርጣሬ ማየታቸውንና በአገዛዙ ለሚወሰድበት ማንኛውም ርምጃ ተባባሪ መኾናቸውን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡

ሌላው መንግሥትና ፓትርያርኩ፣ ማኅበረ ቅዱሳንን ለማፍረስ በሰምና ወርቅነት እየሠሩ መኾናቸውን የሚያመላክተው የዛሬ ሳምንት በጠቅላይ ቤተ ክህነት የማኅበሩ ተቃዋሚዎች ያደረጉትን ውይይትና ያወጡትን የአቋም መግለጫ ስናስተውል ነው፡፡ለመጽሔቱ ዝግጅት ክፍል የደረሰው በድምፅ የተቀረፀ የውይይቱ ሙሉ ክፍል እንደሚያስረዳው፣ ተሰብሳቢዎቹ ማኅበሩን በተመለከተ ያወጡት የአቋም መግለጫ ፤ የዋንኛ የመራሮቹ የባንክ አካውንት ይመርመር ፤ የማኅበሩ ሒሳብ መንግሥት በሚመድበው የውጭ ኦዲተር ይመርመር ፤  ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ንብረቶቹን( ከቀረጥ ነጻ ያስገባቸው ቀላልና ከባድ መኪናዎቹ ሳይቀሩ) ወደ ቤተክህነቱ ይዘዋወሩ፡፡  የንግድ ተቋማቱ (ትምህርት ቤት ፤ ሬስቶራንቶቹ ፤ ንዋየ ቅድሳት ማምረቻ እና ማከፋፈያውን) ያስረክብ ፤ ከምዕመናን በቀጥጣም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚቀበለው አስራት እየፈረጠመበት ስለሆነ እንዳይቀበል ይከልከል ፤ የግቢ ጉባኤ (በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት) እርሱ በሚቀርጸው ትምህርት እንዳይወስዱ መስራት ፤ ተጠሪነቱ ከዋና ሥራ አስኪያጅ ተነስቶ ፤ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ስር አንዱ ንዑስ ክፍል ይሁን… ›› የሚሉ እና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

ከዚህ ሤራ ጀርባ በተቀረፀው ድምፅ ላይ ፓትርያርኩና መንግሥት በትብብር መቆማቸውን የሚያሳየው ፣ የተቃዋሚዎቹ አስተባባሪ መሰብሰቢያ አዳራሹን ለመጠቀም የቻሉት በአቡኑ መልካም ፈቃድ እንደኾነ ከመግለጽ በዘለለ ‹‹ቅዱስ አባታችን በዚህ ተቃውሞ ምክንያት ከሥራ የሚባረር የለም ፤ አይዟችኹ አትፍሩ ብለውናል›› በማለት ሲናገሩ መደመጣቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹ከዚህ ግቢ አቅም ኖሮት የሚያስወጣን የለም እንጂ ካስወጡን መንግሥታችን ቸር ስለኾነ ከእርሱ ቦታ ተቀብለን የራሳችንን ቤተ ክርስቲያን እናቋቁማለን›› እና ‹‹የኦርቶዶክስ እምነት አገልጋዮች ማኅበር እንመሠርታለን›› እስከ ማለት መድረሳቸው ከአገዛዙ ጋራ ያላቸውን የጠበቀ ቁርኝት ያመላክታል፡፡ ተመስገን ቀጥሎም በስብሰባው እንዲሳተፉ ከተቀሰቀሱት 169 አድባራትና ገዳማት እንዲሁም ከ10 ሺህ በላይ ሠራተኞቻቸው መካከል የተገኙት የስምንት አድባራት አስተዳዳሪዎችና 150 ሰራተኞች ብቻ መሆናቸውን አረጋግጫለሁ፡፡

 በሌላ በኩል ደግሞ በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር / ሺፈራው ተክለ ማርያም አዝማችነት በማኅበሩ ላይ የደቦ ዘመቻ ከተከፈተ ሰነባብቷል፡፡ በጥናት ስም በተከታታይ የሚወጡና በየመድረኩ የሚቀርቡ ወረቀቶች ማኅበሩን የኦርቶዶክስ አክራሪ ከማለት አሻግረው ‹‹የግንቦት ሰባት መንፈሳዊ ክንፍ›› ሲሉ ይወነጅሉታል፡፡ በጥቅሉ የእኒህጥናት› ተብዬዎች መደምደሚያ ‹‹ማኅበሩ የትምክህተኞች ምሽግ ነው፤  አክራሪነት አለበት ፤ አመራሩና ሕትመት ውጤቶቹ የፖለቲካ አዝማሚያ ይታይባቸዋል ፤ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጣልቃ ይገባል፤ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዳይኖረው ይሠራል፤ በውጭ ጽንፈኛ የፖሊቲካ ኃይሎች ይዘወራል›› የሚሉ ናቸው፡፡የማኅበሩ አመራሮች እንዲህ ዓይነቱን ውንጀላ በተመለከተ በተለያየ ጊዜ ከአቶ በረከት ስምዖን እስከ / ሽፈራው ተክለማርያም፣ ከአዲስ አበባ የጸጥታ ሓላፊዎች እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ አቶ ፀጋይ በርሄ ድረስ ያሉ ባለሥልጣናትን በቢሮአቸው ተገኝተው ውንጀላው ተቀባይነት ያለው ማስረጃ የማይቀርብበት የሐሰት እንደኾነ ቢያስረዱም መፍትሔ እንዳላገኙ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በግልባጩ በመንግሥት ተቋማት ያሉ የፋክት መጽሔት መረጃ አቀባዮች፣ በግንቦት ወር ከሚካሔደው የሲኖዶሱ መደበኛ ዓመታዊ ጉባኤ በፊት፣ ከኻያ የሚበልጡ የማኅበሩ አመራሮችን ከሽብርተኝነት ጋራ በማያያዝ ለመክሰስና ማኅበሩንም እንደተለመደው በዶኩመንተሪ ፊልም ለመወንጀል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ከሶስት ሳምንት በፊት በአቡነ ገብርኤል ሰብሳቢነት የሚመራው የሃይማኖት ተቋማት ምክር ቤት ስብሰባውን ካጠናቀቀ በኋላ ዶ/ር ሽፈራው አቡኑን ቃል በቃል እንደነገራቸው የተሰማው ነገር ይህን መረጃ የሚያጠናክር ነው፡-

‹‹
በማኅበረ ቅዱሳን አመራር ውስጥ ከሃያ በላይ የተቋዋሚ አባላት አሉ››
‹‹ለዚህ ምንድነው ነው ማስረጃህ? አቅርበው እስኪ እንየው?››
በሀገር ውስጥ ካሉ ጽንፈኛ ጋዜጠኞች በተጨማሪ በስደት የሚገኙና በሽብር ተግባር የተሰማሩ ጋዜጠኞች በአመራርነት አሉበት (የሁለቱን ሰዎችን ስም ጠቅሷል)
‹‹እኛ እስከምናውቀው ማኅበሩ በእንዲህ አይነት ተግባር ራቀ ነው ፤ እናንተ ማስረጃ አለን ካላችሁ አቅርቡና እንየው ፤ ከዚህ ውጪ ይህን አይነት ክስ አንቀበልም..››

በአናቱም የግንባሩ የንድፈ ሐሳብ መጽሔት የማኅበሩን ስም ሳይጠቅስ በደፈናው የወነጀለበትንና ለምን? ብለው የሚጠይቁ ጳጳሳትን በሚከተለው አገላለጽ ማሸማቀቁን ስናስታውስ የማኅበሩ ዕጣ ፈንታ በመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ መቆሙን ያስረግጥልናል፡-

‹‹
በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትርምስና ብጠብጥ ለመፍጠር፣ በኦርቶዶክሶችና ሌሎች ሃይማኖቶች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የሚሞክሩት የደርግና የተለያዩ ትምክህት ኃይሎች ቅሪቶች ናቸው፡፡ እኒኽ የትምክኽት ኃይሎችና አንዳንድ የእምነቱ አባቶች በጋራ ሃይማኖትን በፖሊቲካ ዓላማ ዙሪያ ብቻ መጠቀሚያ አድርገው እየሠሩ ለመኾናቸው 97 ምርጫ በኋላ አንዳንድ በአሜሪካ የሚገኙ ጳጳሳት ቅንጅት በጠራው ሰልፍ ላይ የሃይማኖት አባትነት ካባቸውን እንደለበሱ ከመሰለፍ አልፈው አስተባባሪ ኹነው መታየታቸው በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡›› (አዲስ ራዕይ፤ ሐምሌነሐሴ 2005 ..)

የኾነው ኾኖ ከፍረጃውና ከእስራቱ በተጨማሪ ማኅበሩን ለማዳከም በዋናነት በአገዛዙ የተነደፉት ዕቅዶች ማኅበሩ መሠረቱን ከጣለበት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት ከመከልከልና አባላት ከማለያየት፣ ንብረቶቹን ከመውረስ ጋራ የሚያያዙ ናቸው፡፡ (ከላይ የተመለከተው የተቃዋሚዎች የአቋም መግለጫም ለማኅበሩ የደም ሥር ለኾኑት እኒኽ ኹለት ጉዳዮች ትኩረት የሰጠ መኾኑን ልብ ይሏል)

ስቅለትን ለተቃውሞ
ኢሕአዴግ ወደ መንግሥታዊ ሥልጣን በመጣ ሦስተኛ ዓመት ላይ ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ግቦችና ቀጣይ ርምጃዎች›› በሚል ርእስ ለካድሬዎች በበተነው ድርሳን (በአቶ መለስ እንደተዘጋጀ ይገመታል) ይህን አሁን የተነጋገርንበትን ሃይማኖታዊ ተቋማትን ለሚያቅዳቸው ሥልጣንን የማራዘሚያ አማራጮች ስለመጠቀም ካወሳ በኋላ ተቋማቱን ለሥርዓቱ ፖሊሲዎች እንዲታመኑ ማድረጉ ዋነኛ እንደኾነ ያሠምርበታል፡፡ ይህ የማይቻል ከኾነ ደግሞ፣ እስከ ከፍተኞቹ መንፈሳውያን መምህራን ድረስ ዘልቆ በመግባት ሃይማኖቶቹን መምራት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ግብ መኾን እንዳለበት ያው ሰነድ በግልጽ ቋንቋ ይናገራል፡፡ እንግዲህ ከመጅሊሱ እስከ ማኅበረ ቅዱሳን ያየነው መንግሥታዊ አፈና የዚህን ሃያ ዓመት የሞላው የተጻፈ ሐሳብ መተግበርን ነው፡፡
ግና፤ ከዚኽ ቀደም በተጻፈ ነውረኛ ሐሳብ ትግበራ ፊት ከኹለት ዐሥርት በላይ ህልውናውን ለማቆየት የተጋው ማኅበረ ቅዱሳን፣ ከላይ በሚገባ በጠቀስኋቸው አሳማኝ መረጃዎችና ተጨባጭ ኹነቶች በተከታታይ መከሠት መጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደደረሰ ተመልክተናል፡፡ በዚኽ አስቸጋሪ ወቅት ደግሞ መነሣት የሚኖርበት አስቸጋሪ ጥያቄ፣ እንዴት ይህን ማኅበር ወደ ቀጣዩ ትውልድ ማሻገር ይቻላል? የሚለው ሲኾን ምላሾቹም ሁለት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የማህበሩ አመራሮችና አባላት እስከዚች ቀን እያደረጉ ያለው የውስጥ ለውስጥ የእርምት እንቅስቃሴ ይመለከታል፡፡  በሃይማኖቱ ተቋማት በኩል ለዓመታት ሲሞከር የቆየው ይህው አማራጭ እንደ አስተዋልነው ማኅበሩን ሞት አፋፍ ላይ ከመድረስ ሊታደገው አልቻለም፡፡ ስለዚህም ወደ ሁለተኛውና ዋንኛ መፍትሄሔ አማራጭ መሻገር ግድ የሚል ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ ስጽፍ ለማስረዳት እንደሞከርኩት  የማኅበሩ አመራሮች አባላትና ደጋፊዎች ወደ አደባባይ በመውጣት ማኅበራቸውን ብቻ ሳይሆን ሕልውናቸውንና ህያውነታቸውን የመሰረቱበትን ሐይማኖት ለማውደም የሚተጋውን ስርዓት በሰላማዊ አመጽ  መናድ ብቸኛው  የዚህ አስቸጋሪ ጊዜ  መሸጋገሪያ መንገድ ነው፡፡ በዋናነት የተማሩ ከተሜ ወጣቶችን በአለማዊ ሆነ በትምህርተ ሃይማኖቱ የማይታሙ ዜጎችን የያዘው  ይህ ማኅበር  ፊቱ በተገተረው  ኢህአዴግ ላይ  በሕጋዊ እና  ሰላማዊ እምቢተኝነት  ከማመጽ  የተሻለ አማራጭ እንደማይኖረው የሚረዳ ይመስለኛል፡፡

‹‹ችግሮች ሁሉ የየራሳቸው በጎ ገጾች አሏቸው›› እንዲሉ፣ ማኅበሩ የደረሰበት ይህ ፈታኝ ጊዜን ተከትለው የሚመጡ ሁለት ወቅቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው፣ በቀጣዩ ወር የሚታሰበው የስቅለት ቀን ነው፡፡የሃይማኖቱ ተከታዮች በሙሉ በየቤተክርስቲያኒ የሚውሉበት ይህ በዓል ፤ አገዛዙ እጁን ከማኅበሩ ላይ እንዲያነሳ ለመጠየቅ የተመቸ ቀን መሆኑን ማስታወስ  አባላቱን አሳንሶ መገመት እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡  ኹለተኛና በእጅጉ የተሻለ ነው ብዬ የማስበው ጊዜ ደግሞ ቀጣዩን የ2007 ዓ.ም. ምርጫን ነው፡፡ ለየትኞቹ የሕገ መንግስት ሃሳቦች አልያም የሞራል እሴቶች  የማይገዛው ኢህአዴግ  ፤ በሃይማኖቱ ላይም ሆነ በማኅበሩ ላይ የዘረጋውን የረከሰ እጅ  እንዲያነሳ ያለው ብቸኛ አማራጭ  ሕዝባዊ አመጽ መሆኑን እስከመተማመን ድረስ  ፤ ከዓመታዊ የንግስ በዓላት ጀምሮ ያሉ መድረኮችን በእቅድ ለመጠቀም የዝግጅቱ ጊዜ ዛሬ ነው፡፡  ይህ አይነቱ የተቃውሞ እንቅስቃሴ  ፤ ካነሳው ርዕሰ ጉዳይ አኳያ  የማኅበሩን መኖር የሚሹ ሁሉ ቀጣዩን የምርጫ ወቅት ለማስገደጃነት የመጠቀም ተመክሮዎቻቸውን ተፈላጊው ብቃት ላይ እንደሚያደርሰው  አምናለሁ፡፡ ጥቂት ሊባሉ የማይችሉ አባላቱ የምርጫውን ተጨማጭ እድል መንግሥታዊ ተቋማት በማሽመድመድ  ጭምር እንዴት ስርዓቱን ወደ መቃብሩ ማሻገር እንደሚያውቁ ስንገነዘብ ፤ ቀሪው ጉዳይ ‹‹ሃይማኖታችሁን ተከላከሉ›› ብለው ላስተማሩት ቅዱሳን መጻሕፍትና ለሰማያዊው መንግሥት የመታመን ብቻ እንደሆነ እንረዳለን፡፡

ይህ ጽሁፍ ያለ ምንም ማስተካከያ ቀርቧል



15 comments:

  1. 1. ‹‹የአፍራሽ ግብረ ኃይሉን ጡንቻ ለመመከት ሁሉም በያለበት ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል ፤ .....››
    2. ‹‹ይህ የአንድ ማኅበር ጉዳይ ሳይሆን አንዲት ቤተ ክርስቲያንን የማፈራረስ ስም አጠራሯን የማጥፋት ሴራ ነው.....››
    3. ምንም ጥርጥር የለውም "አቡነ" ማቲያስ ከ"አቡነ" ጳውሎስ ይብሳሉ !!!!!
    4. አብዛኛው ሕዝበ-ክርስቲያን ይህን መረጃ እንዲያገኝ ሁላችንም እንረባረብ!!!!
    5. ከሁሉም በላይ ሁላችንም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በፅናት የምንቆምበት ወሳኝ ወቅት ቢኖር ይህ ነው!!!!

    ReplyDelete
  2. ወልደአማኑኤልMarch 30, 2014 at 12:28 PM

    የ ማሕበረ ቅዱሳን አገልግሎት ከ አግዝአብሔር ሰለሆነ ለግዜው አስፈሪ ቢመስለም በፈጣሪ ዘንድ ግን ያማረ የተወደደ ሰለሆነ ማንም በፈልገው ግዜ ተነሰቶ ሊያስቆመው ሊያፈርሰው አየችልም ጊዜው የሰይጣን እና የገብራበሮቹ መስሎአቸው ከሆነ መቃብራችሁን አርቃቹህ አትቆፍሩ

    ReplyDelete
  3. የኢህአዴግ የመጨረሻ መጀመሪያ?

    ReplyDelete
  4. እግዚያብሔር ይረዳናል ! ትጉና ፀልዩ!

    ReplyDelete
  5. This is what I was certainly expecting from TLF. Unless God does not need the service from Mahebere-Kidusan to the church, this won't become a reality. If becomes a reality, I would say it is the permission of God for members of Mahebere-Kidusan to off load the burden of responsibilities for fulfilling the gaps because of the weakest admin in the church.

    ReplyDelete
  6. GOD created Mahibere Kidusan not to challenge the complete distractive role of durg which end in self distraction rather to challenge the venom of the longest snake ever the church, EPRDF, in distracting the church....These is WHAT Aregaw Berhe said in their TEXT..... As the initial snake devoid from heaven will this snake too

    ReplyDelete
  7. የሚገርመው አላማቸው አለማዊ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እንኳን እንደዚህ ስለ ቤተክርስቲናችን መረጃ ሲኖራቸው እኛ በቤቱ የምንኖር ዝም ብለን የምንመላለስ ክርስቲኖች ልብ አለማለታችን በጣም ነው የሚገርመው…… አስኪ በየቤተክርስቲኑ በተለይም በትልልቆቹ የተሰማሩትን መነኩሴ መሳይ አስተዳዳሪዎችን ተመልከቱ ለካ ገንዘቡን በይፋ እየዘረፉ ፎቅ ስሰሩ፣ መኪና ሲገዙ እንዴው አንድ መነኩሴ እንዲህ ሲሆን እንኳን ሰው እግዚአብሔር ምን ይለናል ብለው የማይፈሩ ለምንድን ነው ብየ አስብ ነበር ለካ የነሱ አላማ ከመዝረፉ ባሻገር የቤተክርስቲናችንን ተቀባይነት ከህዘቡ ለማራቅ ነው…. ለዚህም እኮ ነው በየሰፉ፣ በዘር የሚከፋፍሉን…. ክርስቲያኖ ሌሎች በአለም ያሉት እህት አቢያተ ክርስያናት አሁን እንዲህ ከሥራት ውጭ የሆኑት ልክ እንደዚህ አይት ሥራ ተሰርቶባቸው ነው ስለዚህ ልንነቃ ይገባናል….. በተለይም አብዛኛው ሰው መረጃ ላይደርሰው ስለሚችል እያነበብን ፕሪንት እያደረግን ለሁሉም ክርስቲያን ማሳወቅ አለብን…… ማኅበረ ቅዱሳን እኮ በልቦናችን ያለ እጂ ህንፃ ላይ የተቀመጠ አይደለም በየአመቱ በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ በየዓመቱ የቤተክርስቲንን ትምርት የተማርን ችግሯን የተረዳን በሚሊዮኖች የምንቆጠር በሀገር ቤት ብቻ ሳይሆን በአለም የተሰማሩ በሥራቸው አንቱ የሚባሉ ናሳን ጭምር የሚመሩ ትልዶችን ያቀፈ እኮ ነው……

    ReplyDelete
    Replies
    1. "ማኅበረ ቅዱሳን እኮ በልቦናችን ያለ እጂ ህንፃ ላይ የተቀመጠ አይደለም"
      Thank you wondime. This is what the ruling party did not understand.

      Delete
  8. ‹‹ሃይማኖታችሁን ተከላከሉ››

    ReplyDelete
  9. በሃይማኖቱ ላይም ሆነ በማኅበሩ ላይ የዘረጋውን የረከሰ እጅ እንዲያነሳ ያለው ብቸኛ አማራጭ ሕዝባዊ አመጽ.......

    ReplyDelete
  10. ከኛ ጋራ ያለው ከሁሉም ይበልጣል

    ReplyDelete
  11. ይህ የውዱ ወንድማችን የተመስገን ድመፅነው። ብእርህ ከፍ ይበል!!!!

    ReplyDelete
  12. This time is the end of the ruling TPLF. No one will touch our church. I can say every Orthodox christian who attended college or university education is a member of Mahibere Kidusan. These huge population is now accused of terrorist. Good, TPLF has unlimited right to say and do what ever they want. But time is coming to grave itself.

    ReplyDelete
  13. ከኛ ጋራ ያለው ከሁሉም ይበልጣል

    ReplyDelete
  14. KFTARI EN KWEYANE MAN YEBLTAL ?? HULUME ZEM BELO BELTO METGNATE SELEHON FETENAW BEZTUAL WEYANE MNME AYMTAM EGNA YEMNTE SEW KEHONEN.........

    ReplyDelete