Wednesday, July 2, 2014

‹‹አንቀናጅ ፤ አብረንም እንሥራ››

 የማኅበሩ መልዕክት ከሚለው ገጽ
ሐመር መጽሔት የተወሰደ
ግንቦት 2006 ዓ.ም

ማኅበራችን የአገልግሎት ማኅበር ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር አስፈላጊነቱን አምኖ ፤ የአገልግሎት መስመሩንም በደንብና መመሪያ አስምሮ በመፍቀድ ያቋቋመውም ከዚህ አገልጋይነቱ የተነሳ ነው፡፡ በመኾኑም ማኅበሩ በይፋ ከተመሰረተበት 1984 ዓ.ም ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኗን  በአባላቱ ሞያ ፤ ጉልበትና ገንዘብ እያገለገለ ለዛሬ ደርሷል፡፡ ሕዝቡን ለአገልግሎት በሚጠራና በሚያተጋ አምላክ ፈቃድም ወደፊት አገልግሎቱን እንደሚቀጥል ያምናል፡፡

ሐዋርያዊት በኾነችው ቤተ ክርስቲያን ሥር ለአገልግሎት የቆመው ማኅበራችን ፤ አገልግሎት የጋራና በምትገለገለው ቤተ ክርስቲያን ዕቅፍ ሥር ያሉ ሁሉ ሊተባበሩት የሚገባ መኾኑን በአፅንዖት ያምናል፡፡ ይህንንም ከምስረታው ጀምሮ በተግባር ሲገልጥ ቆይቷል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ዕቅፍ ውስጥ በመኾኑ ከሚመስሉትና ዓላማውን ከሚጋሩት ማኅበራትና አካላት ጋር ልዩ ልዩ ቅንጅቶችን በመፍጠር እያገለገለ ከዛሬ ደርሷል፡፡ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡


የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ዛሬም እንደ ትላንቱ በሀገር ብሎም በዓለም ደረጃ ካለባት መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሓላፊነት አንጻር ቤተክርስቲያን ብዙ አገልጋዮችን ትፈልጋለች፡፡ አገልግሎት ለቤተክርስቲያን ጥቅም የጋራ በጋራ በመኾኑ አንጻርም ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ሊሰጥ የሚገባው አገልግሎት በአገልጋዮች አንድነት ላይ የተመሠረተ ፤ በጋራ መክረውና አቅደው ሊሰጡት የሚገባ መኾን ይገባዋል፡፡

ከዚህ አንጻር ዛሬ በእግዚአብሔር ፍቃድ በልዩ ልዩ ኅብረት በቤተ ክርስቲያኗ ቅጽር የተሰበሰቡ ማኅበራት በቂ ናቸው ብሎ ባያምንም  ያሉት ጥቃቅን ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው ለመንፈሳዊ አገልግሎታቸው መቀራረብ ፤ መመካከርና አብሮ አቅዶ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው በእጅጉ ያምናል፡፡ ማኅበራቱ አብረው ሲያገለግሉ የተበታተነው ኃይል ይሰበሰባል፡፡ በዚህ የጋራ ኃይልም በቁጥርም በይዘትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና እየተወሳሰበ የመጣው የቤተክርስቲያናችን ችግር በአግባቡ መፍትሔ እያገኝ ይሄዳል፡፡ የተጣመመው ይቃናል ፤ የመረረው ይጣፍጣል ፤ የራቀውም ይቀርባል፡፡

በዚህ አጋጣሚ በአምላክ ፍቃድ 22 የአገልግሎት ዓመታትን የዘለቀው ማኅበራችን አሁንም አንዷን ቤተ ክርስቲያን በቅንነት ለማገልገል ያለው ዝግጁነትና ጉጉት ለመግለጽ ይወዳል፡፡ብእሴ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት እንዳለው (መዝ 133 ፤ 1) መንፈሳዊ ቅንአትን ስንቅ አድርገው በልዩ ልዩ መንገድ ለማገልገል የተሰበሰቡ ማኅበራት እንዲገናኙ ፤ እንዲወያዩ ፤ እንዲያቅዱና እንዲሰሩ ለማድረግ የቻለውን ሁሉ ለማድረግ የበለጠ ተዘጋጅቷል፡፡ ይህ የማኅበራችን ጥሪ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተግባራዊ ይኾን ዘንድ ለመተባበር ለሚመጣ ማንኛውም አካልም በሩ ክፍት መኾኑን ይገልጻል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ጥንተ ጠላት ዲያቢሎስ የአገልጋዮቿን ኅብረት አይፈልግም፡፡ በመኾኑም ምንም እንኳን ማኅበራችን ከላይኛው እስከ ታችኛው መዋቅሩ ሁሉ ሲተጋበት የቆየ ቢኾንም ፤ የበለጠ አንቀናጅ ፤ አብረንም እንሥራ ስንል ጥንተ ጠላት ልዩ ልዩ እንቅፋቶችን በመንገዳችን ላይ እንደሚያስቀምጥ ያለፉት ልምዶቻችን ሁሉ ይነግሩናል፡፡ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ትጋትን ፤ ፍቅርን ፤ አንድነትን ይፈልጋል፡፡ በመሆኑም አገልግሎት ከትጋት ፤ ትጋትን ከፍቅር ፤ ፍቅርን ከአንድነት ጋር አስተባብረን በመያዝ ማገልገል ይገባናል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ጥንተ ጠላት ዲያቢሎስ አንድነቱን ስለማይፈልግ ፈተና ያበዛል፡፡ ፍቅርንና ትጋትን  ለማሳጣት ይንቀሳቀሳል፡፡ ነገር ግን ይህንኑ የዲያቢሎስ  የተንኮል ሴራ ጠብቀን እስከተንቀሳቀስን ድረስ ፤ ከማንም በላይ ደግሞ ከላይ ጀምሮ በተዋረድ ያሉ የአበው ምክርና መመሪያ እንዲሁም ጸሎት አጋዥ አድርገን እስከተጓዝን ድረስ እንቅፋቱን ሁሉ አልፈን ሐዋርያት የሰበሰቧትን የሰበኳትን እናት ቤተ ክርስቲያንን እናገለግላለን፡፡ ለዚህም አበው ዛሬም መመሪያ ምክራቸውን እንዳይርቀን ፤ ጸሎታቸውም እንዳይለየን እንጠይቃለን፡፡V   


ወስብሐት ለእግዚአብሔር

3 comments: