Tuesday, July 15, 2014

ዐይናማው ሊቅ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ


እምየዋ! እምየ አድማሱ ጀምበሬ። ምነው በዕድሜ ደርሰን ዐይንዎን አይተን ድምፅዎን ሰምተን በነበር። ዛሬማ ቸልታችንን ዕድሜ ይንሳው እና ኹሉን ነገር ችላ ብለን ለነአባ እንቶኔ ስለተውነው፤ እንደናንተ ያሉቱን ሊቃውንት አሟጥጠን ጨርሰን፤ ቤተ ክርስቲያናችን ቀኝ እና ግራቸውን በማይለዩ ገላግልት እየተወከለች የነውር ማዕድ ትፈተፍት ይዛለች።



ለመልአከ ብረሃን አድማሱ ጀምበሬ መወድስ
እንትኰ በለሰ እመ-በላዕክሙ ወተጋባእክሙ ደርገ ኀበ-ሀለወ ገደላ
አንስርተ-ዲዮስቆሮስ ሊቅ ሊቃውንተ-ጎንደር ገሊላ
እሞትክሙ ሞተ ዘኢዩኤል ወእምየብሰት እስከ-ፍጻሜነ ዜናክሙ ሰግላ
በሊዐ-እክለ-ባዕድ እስመ ውእቱ
ዘበርእሰ-ነቢይ አብቈለ አፈ-አንበሳ-ሐቅል አሜከላ
ማዕዳኒ እንዘ-ነውር በትፍዐ-ጽልዕ መሐላ
በዐልተ-በለስ እፎኑመ ጸውዐተክሙ ለበዐላ
ይገብሩኑ ኅቡረ በዐለ-ሐሤት ወተድላ
ደዋርህ (አርጋብ) ምስለ-አንቄ ወበግዕ ምስለ-ተኵላ
...
++++++++++++++++++++++++++++++
መጋቤ ምሥጢራት የሊቆቹ ዋልታ
መልአከ ብርሃን ማዓረገ ጌታ
ትምህርትን ጋባዡ በሰፊ ገበታ
የመጻሕፍት ምንጭ ማፍለቅ እማይገታ
አንደበተ ዕንቁ አፈወርቅ አለኝታ
የሕግ መሐንዲስ ለሐይማኖት ካርታ
ለተጋፊው ሁሉ መናፍቅ ወስላታ
በሚያስደንቅ ትግል እንዲያ ሲበረታ
በሐምሌ ሃያ አራት ደከመው ተረታ.... ከፍሬ ሊቃውንት

የአንድ ሰው ምስክርነት

መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ለኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን እራሷን እንድትችል ትልቅ ጥረት ካደረጉት የመጀመርያው ተጠቃሽ ሊቅ ነበሩ፡፡ስዝክረ ሊቃውንት የሚለውን መጽሐፋቸውን እያዘጋጁ ባሉበት ወቅት ነው በድንገተኛ ሕመም የአዕምሮ ድካም(ስትሮክ) ምክንያት ሐምሌ 24 19 62 ያረፉት ፡፡የቀብራቸው ስነ-ስርዓት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሊቃውንተ ቤተ-ክርስቲያን እንዲሁም ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት በቅድስት ስላሴ ቤተ-ክርስትያን ተፈጥሟል፡፡ ምኀርካ ክርስቶስ የሚባለው ልጃቸው ታሞ ሞተ ተብሎ ቤተ ዘመድ ሁሉ ሕዝቡ ተሰብስቦ ሲያለቅስ ለቀብር ሲዘጋጁ እሳቸው በማቴዎስ ምዕራፍ ስምንት የተፃፈውን እያነበቡ አዝዝ በቃልከ ይሕየው ወልድዮ ‹‹ልጄ እንዲድን በቃልህ እዘዝ›› ብለው እንባቸውን ሲረጩት ልጁ መነሳቱ ይነገራል፡፡

ስለ ኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን መብት እራሷን እንድትችል የተደረገውን ክርክር በተመለከተም መልአከ ብርሃን አድማሱ ይጠቀሳሉ፡፡የግብፁ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ በጣልያን ጊዜ ጥለው ወደ ግብፅ ሄደው ነበር፡፡ከነፃነት በኃላ ተመልሰው እንዲመጡ ተደረገ፡፡ተመልሰው ሲመጡ ሊቃውንቱ አንቀበልም አሉ ፤ ጠብም ተነሳ፡፡በዚህ ምክንያትከዚህ በኃላ እንለያያለን› የሚል ነገር መጣ፡፡ ሊቃውንቱ ከሁለት ተከፈሉ፡፡ ግማሾቹ ‹‹እንደ ቀድሞው በግብፅ ጳጳስ ይመራ›› የተቀረው ደግሞ ‹‹አይሆንም›› የሚል ሆነ ፡፡የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን እራሷን መቻል አለባት የሚል ሀሳብም መጣ፡፡ክርክሩም ቀጥሎ መጀመርያ ታፈሰ ሀብቴ የሚባሉ በኃላም መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ፤ አስራት ካሳ ፤ አቡነ ቴዎፍሎስ ፤ አቡነ ዮሀንስ ፤ያሉበት ጉባኤ ተፈጥሮ ጉዳዩ በክርክር ከቆየ በኃላ ተፈቀደ፡፡ ኢትዮጵያ እራሷን እንድትችል ሹመቱ ግን ከግብፅ ሆኖ በኢትዮጵ ሊቀ ጳጳስ እንድትመራ የሚል ነበር፡፡   እግዚአብሔር አምላክ እንደ እነዚህ አይነቱን ትልቅ እምነት ከሊቅነት ጋር አጣምረው የሚኖሩ አባቶችን ይስጠን ፡፡አሜን፡፡ 

No comments:

Post a Comment