Sunday, November 2, 2014

ይድረስ ለፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ‹‹ሹመት በአግባቡ ካልሠሩበት ሺህ ሞት ነው››

ጀማል ሐሰን አሊ(የአሁኑ ገብረ ሥላሴ)
አንድ አድርገን ጥቅምት 23 2007 ዓ.ም
  • ‹‹የጥፋት ርኩሰት በማይገባው ሥፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢ ያስተውል››  ማቴ 2415
  • ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ተቃራኒ ሆኖ በርዕሰ መንበርነት መቀመጥ በራሱ አደጋ ነው  ቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና በመጻረርና ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ የሚጎዳ ሥውር ሥራ በመሥራት የክርስቶስን አካል አያድሙ!
  • ‹‹የሚያልፈውንና የሚጠፋውን ፈልገን ብንደክም የማያልፈውንና የማይለወጠውን ብንተው ልብ እንደሌላቸው እንስሳት እንሆናለን፡፡ የዓለምም ፍቅር ነፍስን ታጠፋለች›› ገድለ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን 
  • ምናልባት የምድር ዋጋችሁ የካድሬዎች ጭብጨባና ሙገሳ ሊሆን ይችላል፤ የሆድ ሙላትና የደረት ቅላት፣ የፊት ማማርና አባት መስሎ መታየትን በትርፍነት ሊያስገኝላችሁ ይችላል፡፡ ይህም በምድር የምታገኙት ትርፋችሁ ይሁን እንጂ የሰማዩን ዋጋችሁን ደግሞ መድኃኔዓለም ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡
  • ማኅበሩ በአሁኑ ሰዓት በጥቂቱ ያላነሱ መደበኛ ጠላቶች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ የገዥው መንግሥት ካድሬዎች፣ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን የሆኑ አክራሪ ሙስሊሞች፣ ፕሮቴስታንቶች፣ ተሃድሶዎች፣ የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጠላቶች እነዚህ ሁሉ ዘመቻቸው በማኅበሩ ላይ ነው፡፡
  • ይህን ዓይነት አገልግሎት የሚሰጥ የቤተ ክርስያን አካል የሆነን ማኅበር እርስዎ በሰበሰቧቸው ሕገ ወጥ ስብሰባዎች ላይ ‹‹ከአልሸባብ የተለየ አላደረገም›› ተብሎ ሲወራ ብፁዕነትዎ እንዲያው ትንሽ እንኳን አባትነት አልተሰማዎትም እንዲህ ዓይነቱን ስብሰባ በቤተ ክርስቲያንና በልጆቿ ላይ ለማካሄድ እንዴት ፈቃደኛ ሆኑእንዲያው የቤተ ክርስቲያን ልጆች ከአልሸባብ ጋር ከሚያመሳስሉ ሰዎች ጋር ሲዶልቱ መዋልን እንዴት ኅሊናዎ ቻለው? ብፁዕነትዎ ለዚህ አእምሮዎ አንክሮ ይባል በእውነትአልሸባብ ማለትኮ...............

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ምክንያተ ጽሕፈት፡- ከሙስሊም ወገኖች ጋር በተገናኘ አንዳንድ ጠለቅ ያሉ የጽሑፍ ሥራዎችን ስለምሠራና ንጹሕ ልቡና ላላቸው ሙስሊም ወገኖቻችን ወንጌልን በዘዴ እየሰበኩ ወደ እውነተኛው ክርስትና እንዲመጡ ስለማደርግ በዚሁ አገልግሎቴ ምክንያት የሊቃውንት ጉባዔ አባል ከሆኑ አባቶችና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከሆኑ ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በቅርበት የመገናኘትና በአንዳንድ ነገሮች ላይ መረጃ የማግኘት አጋጣሚው አለኝ፡፡ እናም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይና በቤተ ክህነቱ ውስጥ ስለሚከናወኑ ነገሮች ከምንጫቸው መረጃውን በቀላሉ አገኛለሁ፡፡ ከአሕዛብ ጋር በተገናኘ በምሰጠው አገልግሎት ምክንያት በቅርቡ መሐመድ የሚባል አንድ ወንድሜ ወደ እውነተኛው ክርስትና እንዲገባ ምክንያት ሆኜው ነበር፡፡ እሁድ ጥቅምት 16 ቀን 2007 . ደወለልኝና በቀጠሮ ተገናኘን፣ ነገር ግን ስንገናኝ የቀድሞው መሐመድ የአሁኑ ወልደ ሚካኤል የጠየቀኝ ጥያቄ እንደቀድሞው ስለ ክርስትና እምነት መሠረታዊ ነገር ወይም ስለ አሕዛብ ከንቱነት አልነበረም፡፡ በተናደደ ስሜት ውስጥ ሆኖ ‹‹በአሁኑ ወቅት ከአንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ይልቅ የመስጊድ ሸሆች ይሻላሉ›› አለኝ፡፡ በጣም በድንጋጤ የተዋጥኩ ቢሆንም ምክንያቱን በተረጋጋ ስሜት እንዲነግረኝ ጠየኩት፡፡ በኢንተርኔት ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮችን የሚከታተልበትን የሞባይል ስልኩን አውጥቶ ያነበባቸውን ድረ ገጾችና የፌስ ቡክ ገጾችን በሙሉ እያወጣ አሳየኝ፡፡ ‹‹ይሄኮ በጣም ቀላል ነው ታዲያ›› በማለት በፈገግታ ነገሩን አቅልዬ ላስረዳው ሞከርኩ፡፡ ነገር ግን መሐመድን (የአሁኑን ወልደ ሚካኤልን) እንዲህ በቀላሉ ለማሳመን አቅም አነሰኝ፡፡ ‹‹…መናፍቃንና የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጠላቶች ፓርያርኩን አግባብተው በእጃቸው አስገብተው ማኅበሩን ሊያፈርሱት ነው…›› ‹‹ፓትርያርኩምኮ እየተወያዩና እየወገኑ ያሉት ከሲኖዶሱ ጋር ሳይሆን ከእነዚህ አካላት ጋር ነው…›› ‹‹በአሁኑ ወቅት ከአንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ይልቅ የመስጊድ ሸሆች ይሻላሉ ምክንያቱም ሸሆቹ ቢያንስ ሙስሊሙን ለጠላት አሳልፈው አይሰጡም…›› እያለ የምሬት ንግግሮቹን አወረደብኝ፡፡ ክርስትና ማለት የፈተናና የመከራ ሕይወት መሆኑን፣ ፈተናውም ከእርኩሳን ረቂቅ አጋንንት የሚመጣ መሆኑንና ይኸውም ፈተና በጸሎትና በትእግስት የሚታለፍ እንደሆነ ከዚህ በፊት ያስተማርኩትን መርሳት እንደሌለበት በማስታወስ ትንሽ ካረጋጋሁት በኋላ ሌሎችም ብዙ ነገሮችን አውርተን በሌላ ጊዜ ለመገናኘት በሰላም ተለያየን፡፡

 
ማታ እቤቴ ገብቼ አረፍ ካልኩ በኋላ ግን የዚህ ወንድሜ አነጋገር ውስጤን እረብሾታል፡፡ ለመሆኑ የአሕዛብን ሸሆች የሚያስመሰግን ክፉ ነገር በእኛ አባቶች ዘንድ አለ እንዴ? እውነትም ሙስሊሙን ኅብረተሰብ ለጠላት አሳልፈው የማይሰጡ ሸሆች ባሉበት ወቅት የቤተ ክርስቲያንን ልጆች ለጠላት አሳልፈው የሰጡ ‹‹አንዳንድ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች›› አሉን እንዴ? በተናገሩት ነገር ወይም በሠሩት እኩይ ተግባር ‹‹አንዳንድ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች›› ይሄን ያህል ከአሕዛብ አባቶች ያልተሻሉ ሆነዋልን? ብዬ ራሴን ጠየኩ፡፡ እርግጥ ነው እኔም ወደ ክርስትናው ከመጣሁ ጥቂት ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆኑም በአሕዛብ አባቶች ዘንድ ያለውን ታማኝነት አውቀዋለሁ፡፡ ምንም እንኳን ከላይ ከገዥው አካላት በኩል የሚመጣባቸውን ከባድ ጫና መቋቋም ቢያቅታቸውም የትኛውም የእምነቱ መሪ ሙስሊሙን ኅብረተሰብ አሳልፎ ለጠላት ሲሰጥ አልተመለከትኩ፣ አልሰማሁም፡፡ ስለአሕዛብ መሪዎች ጥንካሬና ታማኝነት ምስክርነት እየሰጠሁ አይደለም ያለሁት-ይልቁንም እነርሱን (የአሕዛብን መሪዎች) እያስመሰገኑ ስላሉት ስለእኛው አባቶች አንዳንድ ነገሮችን ማለት ስለፈለኩ ነው፡፡ 

በዓለም የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እጅግ ዘግናኝ የነበረው ዘመን የወርቅ ምስልን አምላኩ ያደረገው የከሃዲው የዲዮቅልጥያኖስ ዘመን ነው፡፡ የሚወለዱ ልጆችን ክርስትና ለማስነሣት ቤተ ክርስቲያንና አጥማቂ ካህን ከመጥፋቱ የተነሣ እንደ ቅድስት ሣራ ያሉ እናቶች ከአንጾኪያ ግብጽ ድረስ እስከመጓዝና ጡቶቻቸውን እየቆረጡ በደማቸው ልጆቻቸውን እስከማጥመቅ የደረሱበት ዘመን ነው-የዲዮቅልጥያኖስ ዘመን፡፡ በዓለም ላይ ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን ከማቃጠሉም በላይ 9 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ደግሞ በማሠር፣ 47 ሺህ በላይ የሚሆኑ ክርስቲያኖችን በእሳት በማቃጠልና አንገታቸውን በመሰየፍ ምድርን በክርስቲያኖች ደም እንድትጨቀይ ያደረገው ከሃዲው ዲዮቅልጥያኖስ ቢሆንም ለዚህ ጥፋቱ መነሻ የሆነው ግን አንድ የቤተ ክርስቲያን መነኩሴ ነው፡፡ ዲዮቅልጥያኖስ በክርስትና እያመነ ያለ አዲስ ክርስቲያን ነበር፣ እርሱም የቍዝ ንጉሥን ወንድ ልጅ ኒጎሚዶስን በቅዱስ ቴዎድሮስ በናድልዮስ አማካኝነት ከማረከው በኋላ የንጉሡን ልጅ ከአባ አጋግዮስ ዘንድ በአደራ ቢያኖረውም አባ አጋግዮስ ግን በኒጎሚዶስ ክብደት ልክ ወርቅ አስመዝኖ ከአባቱ ከቍዝ ንጉሥ ተቀብሎ ልጁን መልሶ ለአባቱ አሳልፎ ሰጠውና ዲዮቅልጥያኖስን ‹‹የማረከው የንጉሡ ልጅ ሞቷል›› ብሎ ዋሸው፡፡ ንጉሡ ግን እውነቱን ያውቅ ነበር፡፡ መነኩሴው መጽሐፍ ቅዱስንም መትቶ በመማል የውሸት መቃብር አሳየው፡፡ ንጉሡም መነኩሴው በውሸት መጽሐፍ ቅዱስ መትቶ ሲምል ተሰንጥቆ የሚሞት መስሎት ነበርና ምንም ሳይሆን ቢቀር ወርቅ አቅልጦ አምጥቶ ቢያጠጣው ተሰንጥቆ ሞተ፡፡ ዲዮቅልጥያኖስም በክርስቶስ ማመኑን ተወና ‹‹አምላክ ማለት እንዲህ ሰንጥቆ የሚገድል ወርቅ ነው›› በማለት ክርስያኖችን መግደል ጀመረ፡፡ የነገሥታት ልጆች የነበሩት ታላላቆቹ ሰማዕታት እነ ቅዱስ ፋሲለደስ፣ እነ ቅዱስ ፊቅጦር፣ እነ ቅዱስ ገላውዲዮስ፣ እነ ቅዱስ ቴድሮስ በናድልዮስ፣ እነ ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት፣ እነ ቅዱስ ዮስጦስ፣ እነ ቅዱስ አቦሊና ሌሎቹም የከበሩ ኃያላን ሁሉ በዲዮቅልጥያኖስ ትእዛዝ እጅግ አሠቃቂ መከራዎችን እየተቀበሉ በክብር ሰማዕትታቸውን በመፈጸም 49ሺህ ሰማዕታት መሪ ሆነው እንዳለፉ ስንክሳሩ መጽሐፍ ይናገራል፡፡ 

በሀገራችንም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን 40 የመከራና የሥቃይ ዘመን በዮዲት ጉዲት ብታሳልፍም ከዮዲት ከጀርባ ግን የአንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባቶች እኩይ ተግባር ነበረበት፡፡ ይኸውም የእኛው አባቶች ሁለት ጡቶቿን በግፍ ቆርጠዋት ስለነበር በበቀል ተነሥታ ነው ያን ሁሉ መከራ ያጸናችው፡፡ ግራኝ መሐመድም አንዳንድ የቤተ ክርስያናችን አባቶች የግራኝን ወላጅ አባቱን በግፍ ገድለውበት በበቀል ተነሥቶ ነው 15 ዓመት ሙሉ በቤተ ክርስቲያን ላይ ያን ሁሉ መከራና ግፍ የፈጸመው፡፡ የማይካድ ሐቅ ነው ከእያንዳንዱ አስከፊ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጀርባ የእኛው የቤተ ክርስቲያን አባቶች መነሻ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በዘመናችንም ለትውልዱ ጥፋት መነሻ የሚሆን ድርጊት ለመፈጸም ‹‹አንዳንድ አባቶቻችን›› ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ደፋ ቀና ሲሉ ኖረዋል፡፡ ‹‹አባቶች›› ስል እንዲሁ በደፈናው አይደለም-የእኛው አባቶች የመሰሉ አንዳንድ አባቶችን ማለቴ ነው፡፡ ይድረስ ብዬ መልእክቴን የጀመርኩት ለፓትርያርኩ ለአቡነ ማትያስ ስለሆነ የዚህ ጽሑፍ መዳረሻ አድራሻው እሳቸው ናቸው፡፡ 

‹‹
በይድረስ አድራሻ ለፓትርያርክ የሚጽፍ ይኽ ደግሞ የማነው ደፋር!?›› ትሉኝ እንደሆነ እኔም ‹‹አዎን ሺህ ጊዜ ደፋር ነኝ፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ሺህ ጊዜ ብቻ ያይደለ እልፍ አእላፍ ወትእልፊት ጊዜ ደፋር ነኝ›› እላለሁ፡፡ ከዚያ ከአሕዛብ የእርኩሰት ሕይወት ወጥቼ የቅድስና ልጅነትን ባገኘሁባት በቤተ ክርስቲያኔ ጉዳይ ስለሚያገባኝ አዎን ደፋር ነኝ እላለሁ፡፡ ዕለት ዕለት ንስሓ እየገባሁ የአምላኬን የመድኃኔዓለም ክርስቶስን ክቡር ሥጋና ደም በምቀበልባት በቤተ ክርስቲያኔ ጉዳይ አዎን ደፋር ነኝ እላለሁ፡፡ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስያቲያንን መድኃኔዓለም ክርስቶስ በቃሉ ‹‹አካሌ›› ያላት ሲሆን ሐዋርያቱም ‹‹አካሉና ሙላቱ›› መሆኗን ነግረውናል፡፡ ኤፌ 123፡፡ የተለየ የወንጌል መልእክት ይዞ ይህችን የክርስቶስን አካል የሚያደማ (ሕጓንና ሥርዓቷን የሚጥስ) ካለ የሰማይ መልአክም ቢሆን እርጉም እንዲሆን ሐዋርያት በሕጋቸው አጽንተው የለ! ራሳቸው ሐዋርያትም እንኳ ቢሆኑ ፊት ካስተማሩት ትምህርትና ከሠሩት ሥርዓት የተለየ ትምህርትና ሥርዓት መልሰው ራሳቸው ሐዋርያቱ እንኳ ቢያመጡ እነርሱም ራሳቸው ርጉማን እንዲሆኑ በራሳቸው ላይ እርግማንን አውጀዋል፡፡ ገላ 18፡፡ እውነት ነው የክርስቶስን አካል ከማድማት (የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሕጓንና ሥርዓቷን ከመጣስ) ይልቅ በራስ ላይ እርግማንን ማወጅ የተሻለ ነው፡፡
 

በእነዚያ ዓመታት ውስጥ ስንቱ ሕዝበ ክርስቲያን ነው ከክርስቶስ መንጋነት የተለየው? እንደ ሰደድ እሳት በተስፋፋ መልኩ 18 ሚሊዮን በላይ የሆነ ሕዝበ ክርስቲያን ነውኮ ኢየሱሴየስም ሽፋን አምላክ የለሽ የሆነው! እናንተዬ የድሮው ዘመን ሰማዕትነት ይሻል ነበርኮ! ድሮ ድሮ ‹‹ክርስቶስን አምላክ አትበል እርሱን አምላክ ነው ካልክ ግን ሰውነትህን ለእሳት አንገትህን ለሰይፍ›› ነበር የሚባለው፡፡ በዘመናችን ግን ስንቱ ነው በቃል ሰይፍ እየታረደ በተዘዋዋሪ መንገድ አምላኩን ያጣው? ስንት የገሃነም ደጅ የሆኑ የእምነት ድርጅቶች ናቸው የተመሠረቱልን? ከፍትሕ ሚኒስቴር ፍቃድ አግኝተው ሕጋዊ ሆነው የተመዘገቡ 350 በላይ የተለያዩ የእምነት ድርጅቶች በሀገራችን መኖራቸውን ራሱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ነግሮልና፡፡ ቅሉ መድኅን ዓለም ክርስቶስ አንድና አንድ ብቻ ቢሆንም ስንት ክርስቶሶች ናቸው የተፈበረኩልን? እንደማር የሚጣፍጠው ቃለ እግዚአብሔር 365ቱንም ቀናት በሚጎርፍባት ቅድስት ሀገር ላይ ይህን ሁሉ ምንፍቅና ያመጣባት የዲዮቅልጥያኖስ አጋንንት አይደለምን? በቅድስት ቤተ ክርስተያን ያለነውንስ በዘርና በጎጥ እየከፋፈለ የጽድቅ ፍሬን ከምናፈራ ይልቅ በጠላትነት እንድንተያይ የሚያደርገን የዲዮቅልጥያኖስ አጋንንት አይደለምን? ከላይ እስከ ታች ያሉትን አንዳንድ የቤተ ክርስቲያናችንን መሪዎቻችንስ እግዚአብሔርንና ቤቱን ከማገልገል ይልቅ ምድራዊ መንግስትን በማገልገል ቤተ ክርስቲያንን የሚጎዳ ተግባር እንዲፈጽሙ የሚያደርጋቸው የዲዮቅልጥያኖስ አጋንንት አይደለምን? እኔ ግን አዎን በትክክልም እርሱ ነው እላለሁ፡፡ 

በዘመናችን የነበሩ አንድ ታላቅ አባት ጵጵስና እንዲሾሙ ሰዎች ሲያግባቧቸው እኚያ ታላቅ አባት ሹመቱን ለመቃወም የተጠቀሙበት ቃል ‹‹ሹመት በአግባቡ ካልሠሩበት ሺህ ሞት ነው›› የሚል ነበር፡፡ እኔም ወደተነሣሁበት የይድረስ መልእክቴ ልመለስና ይህንኑ መልእክት ማስተላለፍ ፈለግኹ፡፡ ብፁዕ አባታችን አባ ማትያስ ሆይ ሹመትዎ ሺህ ሞት እንዳይሆንብዎ ስፈራሁ ነው ይህን መልእክት ለመጻፍ የተገደድኩት፡፡ ምክንያቱም አባት ብቻ አይደለም ለልጁ የሚስያስበው ልጅም ለአባቱ ያስባልና ነው፡፡ ለምን ይህን እንዳልኩ በዝርዝር አንዳንድ ነጥቦችን ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡ በቅርቡ መስከረም 27 እና 29 እንዲሁም ጥቅምት 5 ቀን 2007 . በጠቅላይ ቤተ ክህነትና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዳራሽ ውስጥ በተካሄዱ ጉባዔያት ውስጥ ብፁዕነትዎ የመክፈቻ ንግግር ማድረግዎን አይተናል፣ ሰምተናል፣ አንብበናል፡፡ አሁንም በዚህ ሰዓት በቅዱስ ሲኖዶስ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ብዙ ደስ የማይሉ ነገሮችን እየተናገሩ መሆንዎን በአካል ካገኘኋቸው ከሁለት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አንደበት ሰምቻለሁ፡፡ ስለዚህ የእርስዎ ዓላማ ምን እንደሆነ ሊገባኝ ስላልቻለ እስካሁንም ሲናገሯቸው የነበሩትን ነገሮች ለመመልከት ተገደድኩ፡፡ ብፁዕነትዎ እርስዎ እስካሁን ከተናገሯቸው ንግግሮች ውስጥ ‹‹የሚሰማኝ ስላጣሁ ከበታች የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ጋር መወያየት አስፈለገኝ›› ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን ቅኝ ገዥ ነው የቤተ ክርስቲያንን ክብርና ሃብት ቀምቷል›› ‹‹ይህ ማኅበር በቁጥጥር ሥር እንዲውል አሳስባለሁ›› ‹‹ቤተ ክርስቲያን ከቅኝ ተገዥነት ትውጣ›› ‹‹እኔ ብቻዬን ሆኛለሁ እኔ ብቻዬን የምሠራው ነገር የለም፤ በዚኽ መግለጫ እንድትሠሩበት ነው የምነግራችኹ›› ‹‹በህግና በሥርዓት የማይመራ ማኅበር አሸባሪ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው›› ‹‹አባ ማትያስ አላበደም፤ መልእክቴን እያስተላለፍኹ ነው ያለኹት፤ መልእክቴን በጸጋ ተቀበሉ ብዬ እማፀናችኋለኹ…›› በማለት ብፁዕነትዎ በተናገሯቸው ንግግሮችዎ ብዙዎቻችን ስንነጋገርባቸው ከርመናል፡፡ በዚህ በፓትርያርኩ ንግግሮችና በያዙትም አቋም ምክንያት ማኅበረ ቅዱሳን ሊፈርስ መሆኑም ሲነገር ሰንብቷል፡፡ ‹‹ፓትርያርኩኮ እንዲህ አሉ…›› ማኅበረ ቅዱሳንን ሊያፈርሱት ነው…›› እየተባለ ሲነገር ነበር፡፡ ይህንንም የሰሙ ብዙ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በድንጋጤም ሆነ በንዴት ብዙ እንደጻፉ አንብቤያለሁ፡፡ እኔ ግን ማወቅ የፈለኩት ብፁዕነትዎ እርስዎ ለምን እንዲህ ሊሉ እንደቻሉ ሳይሆን ይህንን አቋም እንዴት ሊይዙ እንደቻሉና እንዲህስ ብለው እንዲናገሩ ያደረገዎት ምክንያት ምንድነው የሚለውን ነው፡፡ ግን ብፁዕነትዎ እርስዎና ከጎንዎ ያሉ ጆቢራ አማካሪዎችዎ በጋራ ሆናችሁ እናንተ እንዳሰባችሁት ማኅበሩን አፈረሳችሁት እንበልና እሺ ከዚያ በኋላ ምንድነው ማድረግ የፈለጋችሁት? እኔን አሁን ያሳሰበኝ ጉዳይ የማኅበሩ መፍረስ አለመፍረስ ጉዳይ ሳይሆን የዚህ ጥያቄዬ መልስ ነው፡፡ ሲጀመር ማኅበሩን ማፍረስም ፈጽሞ እንደማትችሉ ስለማውቅ ነው መፍረስ አለመፍረሱ አላሳሰበኝም ያልኩት፡፡ ግን ለቤተ ክርስቲያኒቷ ምን አስባችሁላት ነው በቅድሚያ ማኅበሩን ማፍረስ የፈለጋችሁት? ከማኅበሩ ቀጥሎስ የምታፈርሷቸው በየአጥቢያው ጠንካራ ድርሻ ያላቸውን ሰንበት /ቤቶችን ነው? ነው ወይስ እንዳለፈው ሁሉ የቅዱስ ሲኖዶሱንም ልዕልና በተጻረረ መልኩ በማን አለብኝነት እየተንቀሳቀሱ ቅዱስ ሲኖዶሱን ጥርስ የሌለው አንበሳ በማድረግ የቤተ ክርስቲያንን መከራዎች እንደገና ለሁለት ዐሥርት ዓመታት ሊያራዝሙልን ይሆን እንዴ? በመሠረቱ እኔ የማኅበሩ አባል አይደለሁም ነገር ግን ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የሰጠውን፣ እየሰጠ ያለውንና የሚሰጠውን እጅግ ከፍተኛ አገልግሎት ጠንቅቄ ዐውቃለሁ፤ በተግባርም እየታየ ያለ እውነታ ነው፡፡ እውነቱን እውነት፣ ሐሰቱንም ሐሰት ማለት ተገቢና ክርስቲያናዊም ግዴታ ነው፡፡ 

ብፁዕነትዎ ሆይ የጥያቄዬን መልስ ከእርስዎ አልጠብቅም፡፡ ማኅበሩን ካፈረሳችሁ በኋላ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ምን ልታደርጓት እንዳሰባችሁ ምላሹን እኔው እነግርዎታለሁ፡፡ እናም መልሴን እንዲህ ብዬ እጀምራለሁ፡- ብፁዕነትዎ ሆይ እርስዎንኮ በሥውር ሥራውን እንዲሠሩለት ገዥው መንግሥት ነው አምጥቶ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ያስቀመጠዎት እንጂ እውነተኛ አባትነትዎን አምናበት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አልሾመችዎትም፡፡ ይህንን ደግሞ ከማንም በላይ እግዚአብሔር ያውቀዋል፣ እርስዎም ጠንቅቀው ያውቁታል፣ በአቅማችን እኛም ዕናውቀዋለን፡፡ ይሄ ‹‹6ኛው የፓትርያርክ ምርጫ›› ምናምን እያላችሁ ሳትሸውዱን በፊት ገና መርጫው ከመካሄዱ ከሁለት ወር በፊት እርስዎ (አቡነ ማትያስ) 6ኛው ፓትርያርክ ሆነው እንደሚሾሙ በእርግጠኝነት ዕናውቅ ነበር፡፡ ገዥው መንግሥት ‹‹ከፋፍለህ ግዛው›› ፖለቲካዊ አስተሳሰብ የሚመራ ስለሆነ ቅድስት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ‹‹በፍጹም አንድነትና ፍቅር›› መኖርን ስለምንትሰብክ ለገዥው መንግሥት ቤተ ክርስያኒቷ ‹‹እንቅፋት›› እንደሆነችበትና ወደፊትም እንደምትሆንበት ገና በጫካ ውስጥ በትግል ላይ ሳለ ነው የተናገረው፡፡ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላትም ይህንን አምነዋል፡፡ ገዥው መንግሥት በባሕርይው ከፋፍሎና ገነጣጥሎ መግዛትን እንደመርህ ስለሚከተል ‹‹እንቅፋት›› የሆነችበትን ቤተ ክርስቲያንን በተዘዋዋሪ መንገድ በመቆጣጠር በእጁ ስለማድረጉ ፀሐይ የሞቀው አገር ያወቀው እውነት ነው፡፡ ‹‹እንቅፋት›› ደግሞ ከመንገድ መወገድ ስላለበት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎቷን ከማካሄድ ይልቅ በተዘዋዋሪ መንገድ ያላትን ነገር እያጣች እንደ ካሮት ሥር ቁልቁል እንድትጓዝ ተደርጋለች፡፡ ለዘመናት በአንድነቷ ጸንታ የኖረችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በካድሬዎች በኩል እንደራሴ ተደርገው በተሾሙት 5ኛው ፓትርያርክ በአባ ጳውሎስ አማካኝነት ለሁለት ተከፍላ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በሚገኙ ምዕመናን መካከል ከፍተኛ ልዩነት በመፍጠር በአባቶችም መካከል ጥላቻና መወጋገዝ የመጣው ባለፉት 22 ዓመታት ውስጥ ነው፡፡ ፍጹም አንድነትንና ፍቅርን የምትሰብከውን ቤተክርስቲያን በዚህ መልኩ አንድነቷን እንድታጣና ልጆቿም በጠላትነት እንዲተያዩ በማድረግ አቅሟን አሳጧት፡፡ በእምነት ነጻነት ሰበብ መንጋዎቿን ከተቀደሰው ደጅ እያወጡ የገሃነም ደጅ የሆኑ የመናፍቃንን አዳራሽ እንዲሞሉ አደረጓቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትንም በመከፋፈል በፍጹም የጥፋት ጎዳና ላይ እያስጓዙን መሆኑን ብዙዎቻችን ጠንቅቀን እናውቀዋለን፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር ረቂቅ በሆነ ሥልታዊ መንገድ እየተፈጸመ ስለሆነ አብዛኛው ምእመን ገና አልነቃም፡፡ 

ሕግና ሥርዓቱን በመጣስ የቅዱስ ሲኖዶሱንም ልዕልና በመጻረር ብሎም የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ ስልጣን በመጋፋት አባ ጳውሎስ በካድሬዎቻቸው እየተመሩ በማን አለብኝነት የወደዱትን ለመጥቀም ሲሉ አላግባብ በመሾምና በመሻር፣ በመቅጠር በማዛወር የቤተ ክርስቲያኒቱን ገንዘብ ለከፍተኛ ብክነት ሲዳርጉ እንደኖሩት ሁሉ እንዲሁም በብዙ መከራዎች ውስጥ አልፈው የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት ለተማሩት ተገቢ የሥራ መደብ ከመስጠት ይልቅ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደግል ድርጅት በመቁጠር በዘመድ አዝማድ ወይዘሮዎችና አቶዎች ወሳኝ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቦታዎች እንዲይዙ በማድረግ ቤተ ክርስቲያንን ለከፍተኛ ምዝበራና ውርደት ብሎም ለተሃድሶዎች መናኸሪያ ያደረጓት አባ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን የማይነቀል ነቀርሳ ተክለውባት አለፉ፡፡ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 5ኛው ፓትርያርክ በአባ ጳውሎስ አማካኝነት ባለፉት 22 ዓመታት ያሳለፈቻቸውን በርካታ አሠቃቂ መከራዎች በግልጽ ይታወቃሉ፡፡ ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ ስእንደማያጣፍጥ ይታወቃል፡፡ ብፁዕነትዎ አባ ማትያስ ሆይ እርስዎም ወደ ፕትርክናው መንበር የመጡት በመንግሥት ካድሬዎች አጋዥነትና ግፊት የአባ ጳውሎስን ራእይ ለማስቀጠል መሆኑን እናውቃለን፡፡ አባ ጳውሎስም በሕይወት ሳሉ ‹‹ተተኪዬ›› በማለት ከካድሬዎች ጋር እንዳስተዋወቁዎትም እናውቃለን፡፡ ለዚያውም እርስዎም ከካደሬዎችና ከቤተ ክህነቱ ጆቢራዎች ጋር ተደራድረውና ተስማምተው ሹመቱን እንደተቀበሉት ያወቅነው ምርጫው ሳይካሄድ ከሁለት ወራት በፊት ነበር፡፡ ስለዚህ እርስዎ አሁን አያደረጉ ያሉትን ነገር ሁሉ ፓትርያርኩኮ እንዲህአሉ? ለምን እንዲህ አሉ? እንዴት እንዲህ ያደርጋሉ?… ምናምን እያልን ጉልጭ አልፋ በሆነ መልኩ በከንቱ መድከሙ ፋይዳ የለውም፡፡ ምክንያቱም አባ ማትያስ እርስዎ እየፈጸሙ ያሉትና ወደፊትም የሚፈጽሙት የታዘዙትንና ቀድመው የተዋዋሉበትን ነገር ነው፡፡ አብዛኛው ሰው የሚያየው አሁን እርስዎ ማኅበሩን ስለማፍረስ የተናገሩትን ነገር ይሁን እንጂ አባ ማትያስ እርስዎኮ ከተሾሙ በኋላ የመጀመሪያውን የታሪክ ጠባሳዎትን በማኅበሩና በቤተ ክርስቲያን ላይ ያሳረፉት ባለፈው ዓመት ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት 2006 . 200 በላይ ለሚሆኑ ለሊቃውንቱ አብነት መምህራን ትልቅ ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ አዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም እርስዎ ግን በቀጭን ፊርማዎና በፌዴደራል ፖሊስ ማስፈራሪያነት ጉባኤውን ሲያግዱት ብዙዎቻችን በሀፍረት ተሸማቀን በግርምት እጃችንን በአፋችን ላይ ጭነን ነበር፡፡ በማኅበሩና በቤተ ክርስቲያን ላይ ያሳረፉትን የታሪክ ጠባሳዎትንም አንድ ብለን ቆጠርን፡፡ በወቅቱ በአባ ሰረቀ አቀናባሪነትና በፓትርያርኩ ቀጭን ትእዛዝና ፊርማ የታገደውን የጋራ የምክክር ጉባኤ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በፓትርያርኩ የተጻፈውን የእግድ ርምጃ አልተቀበሉትም ነበር፡፡
የጉባኤውም አላማ በኹለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን ዕድገት ሊቃውንቱ የአብነት መምህራን ድርሻ ጎልቶ እንዲወጣ በማድረግ የአብነት መምህራንን የቀለብና የአልባሳት ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲሁም ሊቃውንቱ መምህራን 300 ብር ያለፈ በቂ ደመወዝ ስለማይከፈላቸው ድጋፍ ለማድረግ ነበር፡፡
ጉባኤያቸውን አጥፈው ለሀገር አቀፉ ስብሰባ ከሁሉም አህጉረ ስብከት የመጡ አካል ጉዳተኛና አቅመ ደካማ የሆኑ የቤተ ክርስቲያናችን ምሰሶዎችና ዐይኖች የሆኑ ሊቃውንት በማኅበሩ ዋናው ማእከል /ቤት 3 ቀናት ተሰብስበው በመቆየት የተወያዩ ቢሆንም በኢትዮጵያ ስብሰባ ማዕከል ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር ሳይገናኙና ሕዝቡም በረከታቸውን ሳያገኝ በመቅረቱ በእጅጉ ተቆጭተናል፡፡ ‹‹ጵጵስና መሾምን እንኳን አልፈልግም›› ብለው በበዓታቸው ተወስነው ተማሪዎችን ብቻ በማስተማር ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን ሌት ተቀን የሚተጉ ባለ ጸጋ አባቶች እዚህ እኛው ያለንበት ከተማ ድረስ መጥተው እነርሱን ሕዝቡ ሳያገኛቸውና በረከታቸውን ሳይቀበል በመቅረቱ ብዙዎቻችን በወቅቱ የጨጓራ በሽተኞችም ሆነን ነበር፡፡ በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያናቸን ዐይን የሆኑትን  ሊቃውነቶቻችን የዐይህን ችግር አለባቸው ይኸውም ከጤና አጠባበቅ ጋር በተገናኘ የተፈጠረ ችግር መሆኑ ስለሚታወቅ ማኅበረ ቅዱሳን ሊቃውንቱን የአብነት መምህራኑ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ምሁራን፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ከዓለም ባንክ የወተር ኤይድ እና ከዩኒሴፍ ተወካዮች ጋር በግዮን ሆቴል ስለ ጤና አጠባበቅ ሀገር አቀፉ የምክክር ጉባኤ ሊያካሂድ ነበር የታሰበው፡፡ እነ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራንና ሌሎቹንም 200 በላይ የሆኑ ብርቅዬ የሀገራችንን ሊቃውንት የአብነት መምህራንን ስለ ህልውናችሁ አትወያዩ፣ ስለ ጉባኤያችሁ አትምከሩ፣ ልምዳችሁን አትለዋወጡ፣ በሁሉም የማስመስከሪያ ቤቶች ወጥ አሠራር አትዘርጉ፣ የቤተ ክርስቲያኒቷ ምሰሶዎች እናትነተ መሆናችሁን ዐውቆ ሕዝበ ክርስቲያኑ ለአብነት /ቤቶች የበኩሉን አይርዳችሁ…. በማለት ሊቃውንቱን አትሰብሰቡ፣ አትመካከሩ፣ ችግር አትፍቱ ብሎ ማገድ እምቢ ካላችሁ ግን ‹‹ለመንግሥት እነግርባችኋለ›› ብሎ መንግሥትን ማስፈራሪያ በማድረግ ዐይናቸው እንኳን ማየትም ለማይችሉ ሊቃውነት አባቶቻችን ጉዳኤያቸውን ከልክሎ በእነርሱም ላይ የግልባጭ ደብዳቤ ለፌዴራል ፖሊስና ለብሔራዊ ደህንነት መጻፍ ይሄ የሰይጣን ሥራ እንጂ ‹‹ቅዱስ›› ተብሎ ከሚጠራ ሰው የሚጠበቅ አልነበረም፡፡ ጉባኤውም ባለመካሄዱ ምናልባት ሰይጣን ተጠቅሞ ይሆናል እንጂ የተጎዳችው ግን ቤተ ክርስያናችን ናት፡፡ 

የማኅበሩ ጥናትና ምርምር ማዕከል ባለፈው ስለብራና መጻሕፍት አያያዝና መጻሕፍቱም እየተሰረቁ ከሀገር ስለሚወጡበት ሁኔታ እንዲሁም የመጻሕፍቱን ሕልውና በተመለከተ ምሁራንንና የሚመለከታቸውን አካላት በመጋበዝ የውይይት መርሀ ግብር አዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም አሁንም በፓትርያርኩ ቀጭን የእገዳ ደብዳቤ ምክንያት መርሀ ግብሩ ሳይካሄድ መቅረቱም የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ 

ብፁዕነትዎ እርስዎ የቅርብ አማካሪዎችዎ ያደረጓቸውና በዙሪያዎ የሚያንዣብቡ በርካታ ጆቢራዎች እንዳሉ በግልጽ ይታወቃል፡፡ የቤተ ክርስያን የውስጥ ጠላቶች የሆኑ ‹‹የጨለማው ቡድን አባላት›› እንዲሁም ‹‹ከሙዳየ ምጽዋት ገልባጮች›› ተብለው በሚታወቁት በእነዚህን ጆቢራዎች ምክርና በመንግሥት ካድሬዎች ትእዛዝ አማካኝነት ነው ቅዱስ ሲኖዶሱ የማያውቀውን ሕገ ወጥ ስብስባ መስከረም 27 እና 29 ቀን 2007 . አድገው ማኅበረ ቅዱሳንን ለማፍረስ ሲዶልቱ የሰነበቱት፡፡ ሕገ ወጦቹን ስብሰባዎች ያካሄዱት ቅዱስ ሲኖዶሱ ሳያውቀው ብቻም ሳይሆን መዋቅሩንም ባልጠበቀና ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ባፈነገጠ መልኩ መሆኑን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት /ቤት ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በግልጽ በሚዲያ ተናረዋል፡፡ (አዲስ አድማስ፤ ቅፅ 13 ቁጥር 769 ጥቅምት 1 ቀን 2007 .) ስብሰባው በወቅቱ ‹‹የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ወቅታዊ ኹኔታ የማይገልጽ፣ መዋቅሩን ያልጠበቀና ጽሕፈት ቤታቸው የማያውቀው›› መሆኑን በመግለጽ ዋና ሥራ አስኪያጁ በግልጽ ተቃውሞዎታል፡፡ በወቅቱ አቡነ ማቴዎስ ‹‹መዋቅሩን ሳይከተሉና ከሚመለከተው አካል ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጋራ ሳይመክሩ የሚሠሩት ሥራ ቤተ ክርስቲያኒቱን አደጋ ላይ የሚጥል ነው›› እያሉ ቢመክሩዎትም ብፁዕነትዎ እርስዎ ግን ‹‹የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራት አስተዳዳሪዎችን›› ሰብስበው እጅግ ዘግናኝና አፀያፊ የሆኑ የስድብ ቃላትን ጭምር ሲያደምጡ መዋልዎን ስንሰማ በሀፍረት አንገታችንን ደፋን፡፡
ከምንም በላይ ደግሞ እነዚያ አፀያፊ የስድም ቃላት ለማኅበሩ ቅርብ ናቸው በተባሉና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በሆኑ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አባቶቻችን ላይ የተነገሩ መሆናቸው የበለጠ ኅሊናን ያማል፡፡ በብልግና አፋቸው ከተሳደቡ አይቀር ማኅበሩን ብቻውን ቢሰድቡት ምን ነበረ! ግና እነዚህ ‹‹አስተዳዳሪዎች›› የተባሉ አካላትኮ እነማን እንደሆኑ በሥራቸው በግልጽ እናውቃቸዋለን፡፡ አንድ ወዳጄ እንዳለው እነዚህ አካላት በመንግስት ካድሬዎች ታዘው አይዞአችሁ የተባሉ ሲሆኑ በሥነ ምግባርም የዘቀጡ፣ በሙስናና በስርቆት የደለቡ፣ ሙዳዬ ምጽዋት በመገልበጥና በልማት ስም የተሠሩ የአድባራቱን ሕንፃዎች እያከራዩ ኪሳቸውን የሞሉ፣ ባዶ እጃቸውን መጥተው ቤተ ክርስቲያኒቱን ዘርፈው ቪላ ቤትና መኪና ገዝተው ተንደላቀው የሚኖሩ፣ እነርሱ ውስኪ እየተራጩ በእውነተኞቹ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ላይ የሚያሾፉ፣ በእነ ቅዱስ እንጦንስና በእነ ቅዱስ መቃርስ ቆብ የሚያላግጡ፣ እግዚአብሔርን የማያውቁ የእግዚአብሔር ሰዎች የሚመስሉ የውስጥ ጠላቶች ለመሆናቸው ሥራቸው ከበቂ በላይ ምስክር ነው፡፡
እጅግ የሚገርመውና ኅሊናን የሚያደማው ነገር እነዚህ አካላት በቤተ ክርስቲያን ላይ እንደ መዥገር ተጣብው ገንዘቧን እንደ ደም በመምጠጥ ቤተ ክርስቲያን ለሥጋዊ ጥቅማቸው ብቻ መጠቀማቸው ሳያንስ የቤተ ክርስቲያን መጎዳት የሚያስደስታቸው መሆኑ ነው፤ ማለትም የዶግማዋና የቀኖናዋ መፋለስ፣ በመናፍቃንና በተሐድሶዎች ዘመቻ ምክንያት የክርስቶስ መንጋ መበተን የሚያስደስታቸው መሆኑ ነው፡፡



5 comments:

  1. ለዘመናት በአንድነቷ ጸንታ የኖረችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በካድሬዎች በኩል እንደራሴ ተደርገው በተሾሙት በ5ኛው ፓትርያርክ በአባ ጳውሎስ አማካኝነት ለሁለት ተከፍላ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በሚገኙ ምዕመናን መካከል ከፍተኛ ልዩነት በመፍጠር በአባቶችም መካከል ጥላቻና መወጋገዝ የመጣው ባለፉት 22 ዓመታት ውስጥ ነው፡፡

    ReplyDelete
  2. ‹‹ሹመት በአግባቡ ካልሠሩበት ሺህ ሞት ነው››

    ReplyDelete
  3. Esu egzabiher yastekakilew enji yegnas neger alikolinal . . . . bicha Dingil mariyam libona tistachew kemalet wuch min elachewalehu.

    ReplyDelete
  4. እጅግ ያሳዝናል
    እነዚህ ‹‹አስተዳዳሪዎች›› የተባሉ አካላትኮ እነማን እንደሆኑ በሥራቸው በግልጽ እናውቃቸዋለን፡፡ አንድ ወዳጄ እንዳለው እነዚህ አካላት በመንግስት ካድሬዎች ታዘው አይዞአችሁ የተባሉ ሲሆኑ በሥነ ምግባርም የዘቀጡ፣ በሙስናና በስርቆት የደለቡ፣ ሙዳዬ ምጽዋት በመገልበጥና በልማት ስም የተሠሩ የአድባራቱን ሕንፃዎች እያከራዩ ኪሳቸውን የሞሉ፣ ባዶ እጃቸውን መጥተው ቤተ ክርስቲያኒቱን ዘርፈው ቪላ ቤትና መኪና ገዝተው ተንደላቀው የሚኖሩ፣ እነርሱ ውስኪ እየተራጩ በእውነተኞቹ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ላይ የሚያሾፉ፣ በእነ ቅዱስ እንጦንስና በእነ ቅዱስ መቃርስ ቆብ የሚያላግጡ፣ እግዚአብሔርን የማያውቁ የእግዚአብሔር ሰዎች የሚመስሉ የውስጥ ጠላቶች ለመሆናቸው ሥራቸው ከበቂ በላይ ምስክር ነው፡፡
    እጅግ የሚገርመውና ኅሊናን የሚያደማው ነገር እነዚህ አካላት በቤተ ክርስቲያን ላይ እንደ መዥገር ተጣብው ገንዘቧን እንደ ደም በመምጠጥ ቤተ ክርስቲያን ለሥጋዊ ጥቅማቸው ብቻ መጠቀማቸው ሳያንስ የቤተ ክርስቲያን መጎዳት የሚያስደስታቸው መሆኑ ነው፤ ማለትም የዶግማዋና የቀኖናዋ መፋለስ፣ በመናፍቃንና በተሐድሶዎች ዘመቻ ምክንያት የክርስቶስ መንጋ መበተን የሚያስደስታቸው መሆኑ ነው፡፡

    ReplyDelete
  5. ‹‹ሹመት በአግባቡ ካልሠሩበት ሺህ ሞት ነው››



    ReplyDelete