Friday, November 21, 2014

ሃና ላይ የተፈጸመው ተግባር የምንኖርበትን ማኅበረሰብ ዝቅጠት የሚያሳይ ነጸብራቅ ነው



ሃና ማለት ይች ናት ፤ በማኅበረሳባችን መካካል በወጡ እኛን በመሰሉ ሰዎች ለ5 ቀናት የአስገድዶ መድፈር ተካሂዶባት ህይወቷን ያጣችው ሃና ፤ እግዚአብሔር ነፍሷን ያሳርፍ ፤ ይህን ከመሰለ  ከእምነታችንና ከባህላችን ያፈነገጠ የረከሰን ተግባር  ወደፊት ላለመስማትም ሆነ ላለማየት ሁላችን ሃላፊነታችንን እንወጣ፡፡ ለቤተሰቦቿና ለጓኞቿ መድኃኒዓለም መጽናናትን ያድልልን፡፡

ሃና ላይ የተፈጸመውን  ተግባር  በእግዚአብሔር አምሳል ከተፈጠረ ሰው ተደረገ ለማለት ይከብዳል ፤ ዘመናችን ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ፤ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ገበታ ለመላክ የተሳቀቁበት ፤ ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ልከው እረፍት የማያገኙበት ፤ ጠዋት ማታ ወላጆች ሃሳባቸው ልጆቻቸው ላይ የሆነበት ፤ ኮሽ ባለ ቁጥር ስለ ልጆቻቸው ነፍስ ከስጋቸው የምትለይ ያህል ድንጋጤ የሚፈጠርባቸው ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር የደጋግ አባቶቻችን ጊዜን ይመልስልን›› ከማለት ውጪ ምን እንላለን፡፡ ከሰሞኑ በሃና ላይ የተፈጸመው ድርጊትን ሰምቶ ያላዘነ ፤ ያልተከዘ ፤ ለማያውቃት ወጣት ያላለቀሰ ፤ በድርጊት አድራጊዎቹ ያልተናደደ ፤ ያልተበሳጨ ፤ ጨጓው ያልተላጠ ሰው የለም፡፡ ግን ሁሉም ‹‹ጅብ ከሄደ….›› ሆነና ከቁጭትና ከንዴት በዘለለ መልኩ ልጅትን በህይወት ሊታደጓት አልተቻላቸውም፡፡ ምን ዋጋ አለው እነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ ፍርድ ቤት 20 ዓመት ቢፈርድ?  ምንስ ዋጋ አለው ግፍ አድራጊ ወጣቶች ላይ እድሜ ልክ ቢፈረድ? ግፍ አድራጊዎቹ የማይሽር የእድሜ ልክ ጠባሳ ቤተሰብ ላይ ፤ ጓደኛ ላይ ፤ ሀገር ላይ ጥለው የትኛው ፍርድ ይሆን ይህን ጠባሳ ሊሽር የሚችለው? 

ዘመናችን ይህ ነው ፤ የማናውቃቸው እነርሱም የማያውቁን ግፈኛ ልጆችን ከመካከላችን እያሳደግን ለበለጠ ወንጀል እያዘጋጀናቸው የምንገኝ እኛው ነን ፡፡ ሁሉም በእምነቱ በስነምግባር ፤ በፈሪሃ እግዚአብሔር ልጆቹን ኮትኩቶ ለራሳቸው ፤ ለቤተሰባቸው ቀጥሎም ለሀገራቸው ጥሩ ዜጋ ይሆኑ ዘንድ እስካላዘጋጀ እና ሃላፊነቱንም እስካልተወጣ ድረስ ወደፊት  ሃና ላይ የተፈጸመው ድርጊት የሚፈጸምባቸው የእህቶቻችንን ዜና ላለመስማታችን እርግጠኞች ሆነን ማናገር አንችልም፡፡  ሃና እህታችን ናት ፤ ሃና ልጃችን ናት ፤ ሃና ብዙ ነገራችን ናት፡፡ አሁን ያለንበት ማኅረሰብ በመሀል አዲስ አበባ ፤ የማኅበረሰቡ ንቃተ ህሊና አድጓል በሚባልበት ፤ የመረጃ እጥረት በሌለበት   ይህን ያህል ጭካኔ የተሞላበት ተግባር መፈጸም ከቻለ ሌላው ከከተማና ከሚዲያ የራቀው ማኅበረሰብ ከዚህ የባሰ ተግባር ቢፈጽም ምን ይገርም?  ሃና ላይ የተፈጸመው ተግባር የሚያሳየን ማኅበረሰባችን ምን ያህል ከእምነቱ ፤ ከባህሉ ፤ ከትውፊቱ እንዳፈነገጠና ሌላኛውን የእኩሰት ጫፍ እንደረገጠ ነው፡፡ 

ቤተሰብ ልጆቹን በአግባቡ በእምነትና በስነምግባር ቢያሳድግ ፤ የሃይማኖት ተቋማት እንደ እምነት ተቋምነታቸው ምዕመኖቻቸውን በመልካሙ መንገድ ቢያሰማሩ ፤  ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን በስነምግባር የታነጹ ተማሪዎችን ቢያወጡ ማኅበረሰቡም እንደ ማኅበረሰብ ራሱን ከመጥፎ ነገሮች መጠበቅ ቢችል ዛሬ ሃና ላይ የተፈጸመውን ነገር መስማት ባልቻልን ነበር፡፡

ለቤተሰቦቿና ለጓኞቿ መድኃኒዓለም መጽናናትን ያድልልን

No comments:

Post a Comment