Friday, December 19, 2014

በባህርዳር የሚገኝው መስቀል አደባባይ ታቦት ማደሪያ ‹‹ለልማት ይፈለጋል›› መባሉን ተከትሎ በተካሄደ ተቃውሞ ሰልፍ የንጹሀን ደም ፈሰሰ


አንድ አድርገን ታኅሳስ 11 2007 ዓ.ም


ትላንት እለተ አርብ ታኅሳስ 10 2007 ዓ.ም በባህርዳር ከተማ የሚገኝው መስቀል አደባባይ ታቦት ማደሪያ ‹‹ለልማት ይፈለጋል›› መባሉን ተከትሎ ተቃውሟቸውን ለማሰማት በወጡ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የጸጥታ ሃይሎች በከፈቱት ተኩስ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን እና ቁጥራቸው ያልታወቀ  ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን ያገኝነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ትላንትና ዕለት ከጠዋቱ አንድ ሰዓት የተቀሰቀሰው ድንገተኛ ተቃውሞ ተባሶ መቀጠሉን የገለጹት ምንጮች ሕዝቡ ከባህርዳር ወደ ጎንደር የሚወስደውን ድልድይ በመቆጣጠር ተቃውሞውን መግለጹ ታውቋል፡፡ የተቃውሞ ሰልፈኞቹ መልስ ካላገኙ ድልድዩን እንደማይለቁ አስታውቀው እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል፡፡  የተቃውሞ ትዕይንቱን በሃይል ለመበተን ወታደሮች በከፈቱት ተኩስ ከፍተኛ አደጋ የደረሰ ሲሆን በተለይ ቀበሌ 10 የሚባለው ቦታ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች መገደላቸው ታውቋል፡፡ ተቃውሞውን ተከትሎ ከጎንደር ወደ ባህር ዳር የሚወስደው መንገድ መዘጋቱ ተገልጿል፡፡

የተቃውሞ ትዕይንቱን ለማብረድ ፖሊሶችና የመንግሥት ባለስልጣናት የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎችን በግዳጅ ‹‹ ሕዝቡ ተቃውሞው እንዲያቆም አድርጉ አለበለዚያ እናንተንም እናስራለን›› የሚል ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም አብዛኞቹ የደብር አለቆች ትዕዛዙን አለመቀበላቸው ታውቋል፡፡


ከጥቂት ዓመታት ወዲህ መንግሥት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለዘመናት ስትገለገልባቸው የነበሩ ቦታዎች ላይ በተነሱ ችግሮች በርካታ የእምነቱ ተከታዮች ላይ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ እስከ ህይወት መስዋእትነት ያስከፈሉ ድርጊቶች መፈጸማቸው ይታወቃል፡፡ ከ2 ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ቤተል አካባቢ በሚገኝው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ቦታ ቆርሶ ለመውሰድ መንግሥት ባደረገው ጥረት በወቅቱ የአንድ የፖሊስ አባል ህይወት ሲያልፍ ፤ በቅዳሴ ላይ የሚገኙ ምዕመናን እና ስጋወ ደሙ ለመቀበል በተዘጋጁ ህጻናት እና አረጋውያን ላይ መቅደስ ውስጥ በተተኮሰው አስለቃጭ ጭስ አማካኝነት ረብሻ ከመፈጠሩ በተጨማሪ የቅዳሴ ስርዓቱ መስተጓጎሉ የሁለት ዓመት ትውስታችን ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከዓመት በፊት ጥቅምት 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሦስት ዓመት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያ ቦታ የኢንደስትሪ ዞን ነው በማለት ከፈረሰ በኋላ የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ በጉዳዩ ላይ የሰጡት አስተያይት  ‹‹ይህ ቤተክርስቲያን ለኢንደስትሪ ልማቱ ትልቅ እንቅፋት ነው›› የሚል ነበር፡፡ በሌላ በኩል በደብረዘይት የሚገኝው የባቦጋያ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን 10ሺ ካሬ የሚሆን ቦታ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ይዞታ ላይ በመቁረስ ለአንድ ባለሃብት (ለሪዞርት ማስፋፋያነት) በመስጠት በአካባቢው ምዕመንና ቦታውን ቆርሰው በሰጡት የመንግሥትና የቤተክህነት ሰዎች አማካኝነት ከፍተኛ ውዝግብ መነሳቱ ይታወቃል፡፡

በደቡብ ክልል በደራሼ ልዩ ወረዳ ዋና ከተማ የሆነችው ጊዶሌ ላይ የሚገኝው የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስያን መንገድ ለመስራት ማስተር ፕላኑ ይነካዋል በሚል ምክንያት የወረዳው አስተዳዳሪዎች የመንገድ ስራን አስታከው ቤተ ክርስቲያኑ መፍረስ እንዳለበት ያስገነዘቡት በወርሃ የካቲት  2004ዓ.ም ነበር፡፡ በወቅቱ ይህን የሰማው የአካባቢው ምዕመን እና የከተማዋ መስተዳድር በሁኔታው ፍጥጫ ውስጥ በመግባታቸው ቤተ ክርስቲያኑም ሳይፈርስ መቅረቱ ይታወቃል ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለሊት በጨለማ መናፍቃን እና አክራሪ ሙስሊሞች ሲያቃጥሉ ሰንብተው አሁን ደግሞ ህግን በማስታከክ ‹‹ለልማት›› በሚል አዲስ ፈሊጥ የመንግሥት ባለስልጣናት የቤተ ክርስቲያኒቱ ይዞታ ላይ መነሳታቸው በዚህ ማወቅ ይቻላል፡፡ 

በመሰረቱ የመንገድ እና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች በማንኛውም ሀገር በሚሰሩበት ጊዜ የእምነት ተቋማትን ፤ ትምህርት ቤቶችን ፤ ሆስፒታሎችንና ለሀገር እና ለህዝብ ትልቅ ውለታ ውለው በስማቸው መታሰቢያ የተሰየመላቸውን የሰዎች ሃውልቶችን መነካት እንደሌለባቸው ይታወቃል፡፡  የአገራቸው በጠላት መወረር፣ የሕዝባቸው መገደልና መታሰር፣ የቤተ ክርስቲያናቸው መደፈርና መዋረድ እስከ ሞት ያደረሳቸው የአቡነ ጴጥሮስን መታሰቢያ ለማንሳት በስመ የባቡር ፕሮጀክት ለዚች ሃገር የዋሉት ውለታ ፤ ለአርበኞች ያሳዩት ተጋድሎ ፤ ሕዝቡ በእምነቱ አንድ በመሆን ጠላትን እንዴት መመከለት እንዳለበት ያስተላለፉት መልዕክት ከግምት ውስጥ ሳይስገባ ሃውልቱን እንደ ተራ ሃውልት በመቁጠር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ቤተ ክርስቲያንን  ሳያማከር መንግሥት ሃውልቱ እንደሚነሳና ዳግም በቦታው ላይ ከ2 ዓመት በኋላ እንደሚኖር የባቡር ስራ ፕሮጀክት ስራን በበላይነት የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ሃላፊ አማካኝነት  ነበር በሸገር ሬዲዮ  የተናገረው፡፡

ከዛሬ 15 ዓመት በፊት ህዳር 1992 ዓ.ም አቡነ ጢሞቲዎስ ከ”ምኒልክ መጽሄት” ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ 
‹‹የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መንግስት እንዳይነቀፍ ብለው ቤተ ክርስትያኒቱና ክርስትያኖች መብታቸው ሲነካ ዝም ብለው ካዩ የእግዚአብሔርን አደራ አልጠበቁም ፤ መንግሥትንም ባለመምከራቸው ጎዱት እንጂ አልጠቀሙትም›› በማለት ተናግረው ነበር፡፡ እውነት ነው መንግሥት የቤተክርስቲያኒቱን ቦታዎች ፤ የአምልኮ መፈጸሚያ ስፍራዎች ፤ የምዕመኑን መብት ሲነካ የቤተክርስቲያኒቱ የበላይ ጠባቂዎች በመንግሥት ተግባር አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን ማሰማት ፤ መንግሥት እየሰራ ያለው ስራ አግባብ አለመሆኑን ከስህተቱም እንዲታረም አባታዊ ምክርና ተግሳጽ መስጠት መቻል አለባቸው፡፡ የተዋሕዶ ዓይን የነበሩት አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩም  “መንግሥት ሃይማኖታችሁን ልንካ ካለ  ለሃይማኖታችሁ ፤ ለክብራችሁ ለመብታችሁ መሟገት እንዳለባችሁ እመክራችኋለሁ” በማለት ተናግረው ነበር ፡፡


እግዚአብሔር ሀገራችንን ከክፉ ነገር ይጠብቅልን ፤
 ሕይወታቸውን ላጡ እህት ወንድሞቻችንን ነፍስ ይማርልን

6 comments:

  1. “መንግሥት ሃይማኖታችሁን ልንካ ካለ ለሃይማኖታችሁ ፤ ለክብራችሁ ለመብታችሁ መሟገት እንዳለባችሁ እመክራችኋለሁ”

    ReplyDelete
  2. የዋልድባስ ጉዳይ.........

    ReplyDelete
  3. May God make your wound easy and simple!!!

    ReplyDelete
  4. where is MK?are they only against those priests who raise questions on its structure?shame. all cry just to defend its vested interest including church leaders,MK & politicians. i'm sorry 4 injured and who lost their lives.Let their soul rest in Paradise.

    ReplyDelete
  5. yarfuten ehetochena wenedemoche nefese yemarelene??? bhiwote yalutenem egziabhare yetebkelen!!!!

    ReplyDelete
  6. May the lord of our ancestors be with you at this difficult time. All of you who sacrifice yourselves for the truth will receive your prize from the almighty God.
    " YOU ARETEWAHEDO'S HERO"

    ReplyDelete