Thursday, January 8, 2015

የቤተ ክርስቲያኒቱ የገቢ ማስገኛ ተቋማት ኪራይ የግለሰቦች መጠቀሚያ መኾናቸው ተጠቆመ

  • ሀብትና ጥቅሟን የሚያስጠብቅ የኪራይ ተመን ፖሊሲ የሚወጣበት ጥናት ተጀምሯል
  • የጥቂት አድባራት ሓላፊዎችና ጥቅመኞች እንቅስቃሴ ጥናቱን እንዳያኮላሸው ተሰግቷል
  • የአለቆች የመኪና ሽልማት የሙሰኞች ከለላና ለብልሹነት በር የሚከፍት ነው ተብሏል

 አንድ አድርገን ታኅሳስ 30 2007 ዓ.ም
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አንዳንድ ገዳማትና አድባራት፤ የገቢ ማስገኛ ምንጮችና የልማት ተቋማት የኪራይ አገልግሎት ከሰበካ ጉባኤያት ዕውቅናና የወሳኝነት ሥልጣን ውጭ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብትና ጥቅም ለጥቅመኛ የአድባራት ሓላፊዎችና ግለሰቦች ተላልፎ የተሰጠበት መኾኑ ተጠቆመ።

የተሰጠው፣ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና አንዳንድ ገዳማት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ለማስገኘት የተቋቋመው አጥኚ ኮሚቴ ለፓትርያርኩ አቅርቦታል በተባለ የማስታወሻ ጽሑፍ ነው። የከተማው አስተዳደር ለሀ/ስብከቱ አድባራትና ገዳማት ለማምለኪያ፣ ለመካነ መቃብርና ለልማት መገልገያነት የሰጣቸው መሬቶች፣ ለገቢ ማስገኛ በሚል አብያተ ክርስቲያናቱን ተጠቃሚ በማያደርግ የዋጋ ተመንና ሀብቷን ለጥቅመኞች አሳልፎ በሚሰጥ የውል ዘመን ለግለሰቦች እየተከራዩ ስለመኾኑ በጽሑፉ ተመልክቷል።


ግለሰቦች መልሰው በከፍተኛ ገንዘብ እያከራዩ ተጠቃሚ በመኾን ላይ እንዳሉ ጨምሮ የገለጸው ጽሑፉ፣ በአድባራትና ገዳማት ከመሬት፣ ከሕንፃና ከሌሎች ኪራዮች ጋራ ተያይዘው የሚገኙ ጉዳዮች ትኩረት እንዲሰጣቸው አሳስቧል። በይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አጥኚ ኮሚቴው የቀረበው የማስታወሻ ጽሑፍ በቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ ከታየ በኋላ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት /ቤት በኩል ችግሮቹ በዝርዝር እንዲጠኑ በፓትርያርኩ አማካይነት ትእዛዝ መሰጠቱ ታውቋል።

በአስተዳደር ጉባኤው የተወያየበት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ /ቤት ጉዳዩ አሳሳቢና በሀገረ ስብከቱ አንዳንድ አድባራትና ገዳማት ዘንድ ሰፍኖ የሚታየው የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫ መኾኑን በመገምገም በጥልቀት አጥንቶ የሚያቀርብ አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ማቋቋሙ ተጠቅሷል። የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ እና የዕቅድና ልማት መምሪያዎች ዋና ሓላፊዎች እንዲኹም የሀገረ ስብከቱና የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሓላፊዎች የሚገኙበት ኮሚቴው ከታኅሣሥ መባቻ አንሥቶ፣ የጥናቱን ዕቅድና በጥናቱ መካተት የሚገባቸውን ከስድሳ በላይ አብያተ ክርስቲያናት በመለየት ወደ ሥራ መግባቱ ተዘግቧል።

አድባራት መሬቶች፣ ሕንፃዎች፣ የመቃብር አፈጻጸምና ሌሎች የገቢ ማስገኛ ተቋማት ቤተ ክርስቲያኒቱ በምትጠቀምበት አግባብ አገልግሎት ላይ የሚውሉበትን ኹኔታ ማመላከት የኮሚቴው ዋነኛ ዓላማ ሲኾን የሚከራዩበትን ዋጋ፣ የተከራዩበትን ጊዜና የውል ዘመን ጨምሮ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ዘላቂ ጥቅም የሚሰጡባቸውን መንገዶች ማመቻቸት ጥናቱ የሚያተኩርበት ግብ እንደኾነ በማስፈጸሚያ ስልቱ ተዘርዝሯል።

በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነትና በሓላፊነት ስሜት እንደሚሠራ ኮሚቴው አስታውቆ፤ የጥናቱ አፈጻጸም ከግኝቶች፣ ተመክሮዎችና ተግዳሮቶች በመነሣት ወቅቱንና የአሠራር ሒደቱን ያማከለ ማሻሻያ እንደሚደረግና ለዚኽም የማስፈጸሚያ መርሐ ድርጊቱን ለሚመለከታቸው አካላት አስቀድሞ በመላክ ግብረ መልስ የመቀበያ ጊዜ ማስቀመጡን ገልጧል። የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ የሰበካ ጉባኤ አባላት፣ ጸሐፊዎችና ሒሳብ ሹሞች በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ በመገኘት የሚያነጋግራቸው ዋነኛ አካላት ናቸውም ተብሏል።

በአንዳንድ ገዳማትና አድባራት ሓላፊዎች ደረጃና በግል ንግድ ላይ የተሠማሩ ጥቅመኞችን የሚያስቆጣ ስለመኾኑ በችግርነት የለየው ኮሚቴው፤ ለሥራ በሚንቀሳቀስበት ወቅት የልኡካኑን ስም የማጥፋት፣ በተለይም ከመሬትና መሬት ነክ ከኾኑ ጉዳዮች ጋራ ተያያዥነት ባላቸው ግለሰቦች የጥናቱን ዓላማ በአግባቡ ባለመረዳትና በማጣመም ሥራውን የማጥላላት፣ ሕዝበ ክርስቲያኑን ለማነሣሣት የመሞከር፣ የኪራይ ውልና ሌሎች ሰነዶች ጠፍተዋል በሚል ሰበብ የመደበቅ፣ የተፈላጊ አካላት ተሟልተው ያለመገኘትና መሰል ተግዳሮቶች ሊገጥመው እንደሚችል ታሳቢ አድርጓል።

የጥናቱ ውጤት ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚጠቅምና ሀብቷን የሚያስጠብቅ መኾኑን በመገንዘብ የተጣለበትን ሓላፊነት በብቃት ለመወጣት መወሰኑን ያስታወቀው ኮሚቴው፣ እንቅስቃሴውን በመገምገም ሒደቱን በብዙኃን መገናኛ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ግልጽ የሚያደርግበትን የጊዜ ሰሌዳ ከማስቀመጥ ጀምሮ ተግዳሮቶቹን የሚቋቋምባቸውን ስልቶችና አሠራሮች በዝርዝር መንደፉን አመልክቷል። አኹን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተወሰኑ ገዳማትና አድባራት መነሻነት የሚካሔደውና ለቅዱስ ሲኖዶሱ እንደሚቀርብ የሚጠበቀው ጥናት ውጤት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን የመሬት አጠቃቀምና ወጥነት የሚጎድለው የኪራይ ተመን የተመለከተ ፖሊሲ ለማውጣት በግብአትነት የሚያገለግል ነው ተብሏል።

 ዜና፣ በሀገረ ስብከቱ አድባራትና ገዳማት ለአለቆች እየተበረከተ የሚገኘው የመኪና ሽልማት፣ ለአማሳኞች ከለላ የሚሰጥና ለብልሹ አሠራር በር የሚከፍት ነው በሚል በአስቸኳይ እንዲቆም በፓትርያርክ አቡነ ማትያስ መታዘዙ ተሰምቷል። መረጃው እንደሚጠቁመው፣ ልማታዊ ናቸው በሚል መኪና ለአለቆች የሚሰጥበት የሽልማት ሥነ ሥርዓት፤ የሥራ አፈጻጸማቸው ያልተገመገመበትና በሽልማቱ ጉዳይ ግልጽ መመሪያ በሌለበት ኹኔታ የተፈጸመ ነው። በልማታዊነት ስም የሕዝበ ክርስቲያኑ ገንዘብ ለሽልማት የሚውልበት አሠራር እንዲቆም በፓትርያርኩ ተሰጥቷል የተባለው ትእዛዝ፣ የጠቅ/ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለሀ/ስብከቱ በጻፉት ደብዳቤ መመሪያ የተሰጠበት ሲኾን አፈጻጸሙ የሚገኝበትን ኹኔታ መገምገም የአጥኚ ኮሚቴው ተልእኮ አካል እንደኾነ ታውቋል።

Source :- Sendek Newspaper 


1 comment:

  1. Hi there, its pleasant artifle concerning media print, we all know media is a great source of facts.

    ReplyDelete